16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ከነገ በስቲያ በሩሲያዋ ካዛን ከተማ ይጀመራል
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ ጉብኝት ሩሲያ ገቡ።
ፕሬዝዳንቱ በቩኖኮቮ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
ምክክሩ በ2018 የስትራቴጂካዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረሙት ኤምሬትስ እና ሩሲያ በንግድ፣ ኢንቨስተመንት፣ ኢነርጂ እና ሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
የመካከለኛው ምስራቅ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና ፑቲን ምክክር እንደሚያደርጉ ነው የሚጠበቀው።
ኤምሬትስ ሶስተኛ አመቱን ሊይዝ የተቃረበው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በንግግር እንዲቆም ጥረት ስታደርግ የቆየች ሲሆን፥ ሁለቱ ሀገራት ዘጠኝ ጊዜ የጦር እስረኞችን እንዲለዋወጡ በማደራደርም ስኬታማ ተግባር ፈጽማለች።
ሶቪየት ህብረት ኤምሬትስ እንደ ሀገር በተመሰረተች (1971) በስድተኛው ቀን እውቅና መስጠቷ ይታወሳል።
ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላም ሩሲያ በኤምሬትስ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የሀገራቱ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሯል።
ባለፈው አመት በዱባይ በተካሄደው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉብኤ የተሳተፉት ፕሬዝዳንት ፑቲን የኤምሬትስ እና ሩሲያ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ተናግረው ነበር።
ኤምሬትስ በአረቡ አለም የሞስኮ ቀዳሚዋ የንግድ አጋር መሆኗን መግለጻቸውም የሚታወስ ነው።
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በሩሲያ ቆይታቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ስፔስ ቴክኖሎጂ የሀገራቱን ትብብር የሚያጠናክር ምክክር ያደርጋሉ።
ፕሬዝዳንቱ ከነገ በስቲያ ጥቅምት 12 በካዛን ከተማ በሚጀመረው 16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋሉ።