"በእኔና በቤተሰቤ ላይ አንዳች ነገር ቢደርስ ተጠያቂው ፕሬዝዳንት ሩቶ ነው" - ሪጋቲ ጋቻጉዋ
ከስልጣናቸው የተባረሩት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት የተመደቡላቸው የፀጥታ አካላት መነሳታቸውን ተናግረዋል
የ59 አመቱ ጋቹጉዋ ባለፈው ሀሙስ ከስልጣናቸው ተነስተው በኪቱሬ ኪንዲኪ መተካታቸው ይታወሳል
ከስልጣናቸው ተነስተው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነባቸው የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቹጉዋ ደህንነታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ገለፁ።
በምክትል ፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሁሉም ሰራተኞች አስገዳጅ እረፍት እንዲወጡ መደረጋቸውንም ነው ዛሬ ከሆስፒታል ሲወጡ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
ፓለቲካዊ ሻጥር ያለበት ክስ ቀርቦብኛል የሚሉት ጋቻጉዋ፥ "በእኔ ወይም በቤተሰቤ ላይ የሆነ ነገር ቢደርስ ተጠያቂው ፕሬዝዳንት ሩቶ ነው" ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
"ያመንኩት፣ ስልጣን እንዲይዝ የረዳሁት ሩቶ በእኔ ላይ እንዲህ መጨከኑ አስደንግጦኛል” ያሉት የ59 ዓመቱ ጋቹጉዋ፥ ፕሬዝዳንት ሩቶ በ2022 ወደ ስልጣን እንዲመጡ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኬንያ ፓርላማ አባላት ግን ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሰኔ ወር ከታክስ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ ተሳትፎ ነበራቸው ይላሉ።
መንግስትን አጣጥለዋል፤ በሙስና ተዘፍቀዋል በሚሉና ሌሎች ውንጀላዎችም ባለፈው ሀሙስ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ድምጽ ሰጥተውባቸዋል።
ጋቹጉዋ ህገመንግስቱን የመጣስና የጥላቻ ንግግርን ጨምሮ ከቀረቡባቸው 11 ክሶች አምስቱ ተቀባይነት በማግኘታቸው ነበር ባለፈው ሀሙስ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው።
ከትናንት በስቲያ አርብም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪቱሪ ኪንዲኪ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።
የአዲሱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቃለመሃላ ግን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲዘገይ መደረጉ አይዘነጋም።
የኬንያ ፖሊስ ፖለቲካዊ ክስ ቀርቦብኝ የጥበቃ አካላትም ተነስተውብኛል ያሉት ጋቹጉዋ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ አልሰጠም።
የቀድሞ ደጋፊያቸው ከስልጣን ከተነሱ ወዲህ በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን የመረጡት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በዛሬው እለት ባደረጉት ንግግር “ጎሳዊ እሳቤ እና አግላይነት” ይቁም ሲሉ ተደምጠዋል።