አራት ሚስቶችና ሁለት ፍቅረኞች ያሉት ጃፓናዊ 54 ልጆች መውለድ እፈልጋለሁ አለ
የ36 አመቱ ወጣት ባለፉት 10 አመታት ስራ የለውም፤ ከሚስቶቹ በሚያገኘው ገንዘብ 10 ልጆቹን ያሳድጋል
ጃፓናዊው ወጣት “ሴቶችን እወዳለሁ፤ በእኩል ደረጃ መፋቀር ከተቻለ ምንም ችግር አይኖርም” ብሏል
ርዩታ ዋታናብል በጃፓን ሆካይዶ ደሴት ሰሜናዊ ጫፍ ነዋሪ ነው።
የ36 አመቱ ዋታናብል ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ምንም ስራ አላገኘም። ስራ ማጣቱ ከአንድም አራት ሚስቶች አግብቶ፤ ሁለት ፍቅረኞችን ይዞ ከመኖር ግን እንዳላገደው ይናገራል።
ወጣቱ ትዳሩን የሚመራበት ጥሪት አስቀድሞ ቋጥሮ ግን አይደለም፤ ከሚስቶቹ በሚያገኘው ገንዘብ ነው ጎጆውን የሚመራው።
ሳውድ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት እንዳስነበበው የዋታናብል ሚስቶች በአንድ ጎጆ ለመኖር ይስማሙ እንጂ በህጋዊ መንገድ ጋብቻቸውን የፈጸሙና በውልና ማስረጃ የተመዘገቡ አይደሉም።
ከሚስቶቹ 10 ልጆችን ያፈራው ወጣት በአንድ ጎጆ የሚኖረው ከሶስት ሚስቶቹ እና ሁለት ልጆቹ ጋር እንደሚኖር ተዘግቧል።
ስራ የሌለው ዋታናብል እንደ “የቤት እመቤት” ከሚስቶቹ በሚቀበለው ገንዘብ አስቤዛ ይሸምታል፤ ምግብና ሌሎች በቤት ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎችን ይከውናል፤ ህጻናቱንም ይንከባከባል ተብሏል።
የዋታናብል ቤተሰብ ወርሃዊ ወጪ 914 ሺህ የጃፓን የን (6113 ዶላር) ነው። እናም የወጣቱ ሚስቶችና ፍቅረኞች እኩል ይካፈሉታል።
ፍቅረኛው ከስድስት አመት በፊት በስራ ማጣት ድብርት ውስጥ በገባበት ወቅት ጥላው ስትኮበልል በትዳር አፋላጊ ድረገጾች ላይ አጋር መፈለግ መጀመሩን የሚያወሳው ጃፓናዊ ሁለት ፍቅረኞቹን በዚሁ መንገድ ማግኘቱን ገልጿል።
ባለፈው አመት አቤማ ፕራይም ከተባለ የጃፓን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቆይታም “እኔ ሴቶችን እወዳለሁ፤ በእኩል ደረጃ እስከተፋቀርን ድረስ ምንም ችግር አይፈጠርም” ሲል ተናግሮ ነበር።
ርዩታ ዋታናብል ልጆቹን ሲንከባከብና ሚስቶቹ ከስራ ሲመለሱ ጠብ እርግፍ እያለ ሲቀበላቸው የሚያሳይ ምስል ተለቆም መነጋገሪያ ሆኗል።
አራት ሚስቶችና ሁለት ፍቅረኞች ያሉት ወጣት 54 ልጆችን የመውለድ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።
ስኬታማ የትዳር ህይወት እየመራሁ ነው ብሎ የሚያምነው ዋታናብል “የትዳር አማልዕክት” መሆን እንደሚሻ መናገሩም ነው የተዘገበው።