አል አይን በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ሲደርስ ከ2016 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
የአረብ ኤምሬትሱ አል አይን በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋገጠ።
በሩብ ፍጻሜ ፍልሚያው የክርቲያኖ ሮናልዶውን አል ናስር ያሰናበተው አል አይን በግማሽ ፍጻሜው ሌላኛውን የሳኡዲ ክለብ በመርታት ለፍጻሜ ደርሷል።
የእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ በሪያድ ሲካሄድ አስተናጋጁ ቡድን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ኔይማርና አሌክሳንደር ሙትሮቪችን በጉዳት ያላሰለፈው አል ሂላል በሪያድ ያስመዘገበው ውጤት ግን ለፍጻሜ የሚያበቃ አልነበረም።
አል አይን ባለፈው ሳምንት አል ሂላልን በሜዳው 4 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።
ይህም ተከትሎም የኤምሬትሱ ቡድን የአራት ጊዜ የእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን ጥሎ ለፍጻሜው መድረስ ችሏል።
በአርጀንቲናዊው ሄርናን ክሬስፖ የሚሰለጥነው አል አይን በፍጻሜው ከደቡብ ኮሪያው ኡስላን ሃዩንዳይ አልያም ከጃፓኑ ዮኮሃማ ኤፍ ማሪኖስ ጋር ይጫወታል።
የአል አይን የፍጻሜ ተፋላሚውን የሚለየው ጨዋታ በዛሬው እለት ይካሄዳል።
የኤምሬትሱ ክለብ በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ሲደርስ ከ2016 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።