አል ናስር በኤምሬትሱ አል አይን ተሽንፎ ከእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሰናበተ
ሮናልዶ በሪያዱ የመልስ ጨዋታ ጎል ቢያስቆጥርም ክለቡ በመለያ ምት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል
የሳኡዲዎቹ አል ሂላል እና አል ኢትሃድ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል
የሳኡዲው አል ናስር ከእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሰናበተ።
አል ናስር በኤምሬትሱ አል አይን ተሸንፎ ነው ከሻምፒዮንስ ሊጉ ውጭ የሆነው።
አል አይን በአቡ ዳቢ ባለፈው ሳምንት በተደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
በትናንቱ የመልስ ጨዋታ ባለሜዳው አል ናስር 4 ለ 3 ማሸነፍ ችሏል።
ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶም በጭማሪው ስአት ክለቡን መሪ ያደረገ ጎል ማስቆጠር ችሎ ነበር።
ለአል አይን ሞሮኳዊው ሱፊያን ራሂሚ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ሱልጣል አል ሻምሲ በጭማሪ ስአት ሶስተኛዋን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።
የጭማሪው ስአት ውጤት አል ናስርን 4 ለ 3 መሪ ቢያደርግም ድምር ውጤቱ (4 ለ 4) በመሆኑ ቡድኖቹ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርተዋል።
የሳኡዲው ቡድን በሮናልዶ ካስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ውጭ ሶስቱን በመሳቱና አል አይን ሶስቱንም በማስቆጠሩ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ወደ ግማሽ ፍጻሜው መግባቱን አረጋግጧል።
የኤምሬትሱ ቡድን በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ መግባቱን በማረጋገጥ ቀዳሚው ሆኗል።
አል ናስር የተሰናበተባት ሳኡዲ በግማሽ ፍጻሜው አንድ ክለቧ እኝደሚሳተፍ ቀደም ብላ አረጋግጣለች፤ ዛሬ ምሽት አል ሂላል እና አል ኢትሃድ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባለፈው ሳምንት 2 ለ 0 ያሸነፈው አል ሂላል የካሪም ቤንዜማውን አል ኢትሃድ በድምር ውጤት በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው እንደሚደርስ ተገምቷል።