ሮናልዶ በሳዑዲ ሊግ ስለተላለፈበት ቅጣት በሰጠው አስተያየት ምን አለ?
ሮናልዶ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎችን በምልክት በመዝለፍ 1 ጨዋታና 30 ሺህ ሪያል ተቀጥቷል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ “ለሳዑዲ ባሕል ሁሌም ክብር አለኝ” ሲል ተናግሯል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎችን በምልክት በመዝለፍ በሳዑዲ ሊግ የተላለፈበትን ቅጣት ከፈጸመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በሳዑዲ ሊግ የተላለፈበትን ቅጣት የጨረሰው ሮናልዶ “ለሳዑዲ ባሕል ሁሌም ክብር አለኝ” ሲል ከቅጣቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው አስተያየቱ አስታውቋል።
የሮናዶ ቡድን አልናስር አልሻባብን 3 ለ 2 ባሸነፉበት ጨዋታ ማጠናቀቂያ ላይ የተቃራኒ ቡድኑ አል ሸባብ ደጋፊዎች ተጨዋቹን ለማናደድ የሊዮኔል ሜሲን ስም እያነሱ ሲዘምሩ ለነበሩ ደጋፊዎች አስነዋሪ ያልተገባ ምልክት አሳይቷል ተብሏል።
የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሮናልዶ ያደረገውን አሳፋሪ ተግባር አስመልክቶ በሳለፈው ውሳኔው፤ ሮናልዶ የአልሸባብ ክልብ ደጋፊዎችን በመስደብ የሀገሪቱን የእግር ኳስ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 57 ንዑስ አንቀጽ 1 ተላልፏል ብሏል።
ይህንን ተከትሎም የዲሲፕሊን እና የስነ ምግባር ኮሚቴው ክርስቲያኖ ሮናልዶን የአንድ ጨዋታ ቅጣት እና የ30 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የገንዘብ ቅጣት አሳልፎበታል ነው የተባለው።
ቅጣቱን ተከትሎም ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ ሊግ 22ኛ ሳምንት ክለቡ አል ናስር ከአል ሃዛም ጋር ያደረገው ጨዋታ አምልጦታል።
ሮናልዶ በሳዑዲ ሊግ የተላለፈበትን ቅጣት ከጨረሰ በኋላ በሰጠው አስተያየት በውድድሩ ላይ ያሳየው ምልክት ማንንም ለመጉዳት እንዳላደረገ አስታውቋል።
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለ ጉዳዩ በሰጠው ማብራያ “እኔ የሁሉንም ሀገራትን ባህል ሁልጊዜም ቢሆን አከብራለሁ፤ ሰዎች ሁሌም የሚያዩት ነገር ትክክለኛውን ነገር አይደለም” ብሏል።
“ከዚህ በፊት የተናገርኩት እና አሁንም የምደግምለችጉ ነገር ቢኖር ይህንን ምልክት በዚህ ሀገር ውስጥ ድጋሚ እንደማላሳይ አረጋግጥላችዋሁ” ሲል ተናግሯል።
ሮናልዶ “ያደረግኩት እንቅስቃሴ እና ያሳየሁት ምልክት ጥንካሬን እና ድልን ይገልፃል እንጂ አሳፋሪ አይደለም፤ ይህንን አይነቱን የደስታ አገላለጽ በአውሮፓም ለምደነዋል” ብሏል።
ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ “ሁሉንም ክለቦች አከብራለሁ፤ ከጨዋታ ላይ በኋላ የምናሳየው የደስታ ምልክት ጥንካሬን እና ደልን የሚያሳዩ እንጂ አሳፋሪ ነገር አይደሉም” ብሏል።