ሮናልዶ በሳኡዲ ሱፐር ካፕ ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣበት መንገድ አከራካሪ ሆኗል
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች የአል ሂላል ተከላካይን በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል
አል ናስር በሳኡዲ ሱፐር ካፕ ግማሽ ፍጻሜ በአል ሂላል 2 ለ 1 ተሸንፏል
የሳኡዲው አል ናስር ክለብ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትናንት ምሽት ከለቡ ከአል ሂላል ጋር ሲጫወት በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል።
ሮናልዶ በሳኡዲ ሱፐር ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ በተቀናቃኙ አል ሂላል 2 ለ 0 እየተመራ እያለ በ86ኛው ደቂቃ በፈፀመው ድርጊት ነው ዳኛው ቀይ ካርድ የመዘዙበት።
በቀሪ ወሳኝ ደቂቃዎች የአል ናስርን ውጤት ለመለወጥ ሲሯሯጥ የነበረው ሮናልዶ የእጅ ኳስ በፍጥነት ለመወርወር ሲሞክር የአል ሂላሉ አሊ አል ቡላሂ ስላገደው በክርኑ ገፍትሮት በተጫዋቾች መካከል ትርምስ ተፈጥሯል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዋና ዳኛም ፖርቹጋላዊውን አጥቂ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሲሰጡት ለመማታት ሲቃጣ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ሮናልዶ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን እንደሱ እንዲገልፁ ማነሳሳቱም በቀጣይ ተጨማሪ ቅጣት እንዲጣልበት ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
ኦታቪዮ አስቆጥሯት ለነበረችው የአል ናስር ጎል አመቻችቶ ያቀበለቅ ሮናልዶ ከጨዋታ ውጭ ነበር በሚል ዳኛው ጎሉን ሲሽሩ የ39 አመቱ አጥቂ የሰጠው ምላሽም ቢጫ ካርድ እንዲመለከት አድርጎት ነበር።
የአል ናስር አሰልጣኝ ሊዊስ ካስትሮ ሮናልዶ በቀይ ካርድ የወጣበት መንገድ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
ሮናልዶ ድርጊቱን እንዲፈጽም ያስገደደው የአል ሂላሉ ተከላካይ ጸብ አጫሪነት መሆኑን ነው የገለጹት።
የሮናልዶና የተቀናቃኙ ቡድን ተከላካይ አካላዊ ንክኪ በቀይ ካርድ የሚያሰናብት እንዳልነበርና ዳኛው በቪዲዮ የታግዘ ዳኝነት (ቫር) ተመልክተው ሊሽሩት በተገባ ነበር ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የአል ሂላል አሰልጣኝ ዮርጌ ጀሱስም ለአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የፈጸመው ድርጊት ለድል ከመጓጓቱና ሽንፈትን ከመጥላቱ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
“ሮናልዶ በአለማችን ወሳኝ ከሚባሉና ለበርካቶች አርአያ ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ ነው፤ ሽንፈት ያበሳጨዋል፤ እናም ቡድኑ ለመሸነፍ ሲቃረብ ቢበሳጭ ተፈጥሯዊ ነው” ሲሉም አክለዋል።
አል ናስር ሮናልዶ ከወጣ በኋላ በቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥርም 2 ለ 1 ከመሸነፍና ከሳኡዲ ሱፐር ካፕ ከመሰናበት አልዳነም።
በሳኡዲ ፕሮ ሊግ አል ናስርን በ12 ነጥብ በመብለጥ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው አል ሂላል በሳኡዲ ሱፐር ካፕ ፍጻሜ የፊታችን ሀሙስ አል ኢትሃድን ይገጥማል።