በአለ የስነ ጥበብ ትም/ት ቤት የተዘጋጀውና የ”አርበኝነትን ታሪክ” የሚያሳየው አውደ-ርዕይ በጥበብ አፍቃሪያን እየተጎበኘ ነው
አውደ ርዕዩ አጼ ሚኒሊክን ጨምሮ በአጼ ቴዎድሮስ፣አጼ ዮሃንስ እና አጼ ኃይለ ስላሴ የተመሩ የተለያዩ ገድሎች የሚያሳዩ የስነጥበብ ውጤቶች ያሉበት ነው
ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ የሚቆየው አውደ ርዕዩ በቀን 100 የጥበብ አፍቃርያን እየጎበኙት ነው ተብሏል
በአለ የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ትም/ት ቤት የተዘጋጀውና የ”አርበኝነትን ታሪክ” የሚያሳየው አውደ-ርዕይ በጥበብ አፍቃርያን በመጎብኘት ላይ ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 2 የእይታ ክፍት የሆነው አውደ ርዕዩ፤ የየዘመናቱ ስነ-ጥበብ ውጤት የሆኑትና የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ የዘመናት አርበኝነትን የሚያሳዩ የስነ-ጥብብ ስራዎች ያካተተ ነው፡፡
በአለ የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት የስነ-ጥበብና ቪዝዋል ካልቸር መመህር ገረመው ፈይሳ (ፒ.ኤች.ዲ) የአውደ-ርዕዩ ዋና ገዢ ሀሳብ የኢትዮጵያውያን መለያ የሆነው “አርበኝነት” ነው ሲሉ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግሯል፡፡
የስነ-ጥበብና ቪዝዋል ካልቸር መመህሩ ገረመው ፈይሳ አክለው አውደ-ርዕዩ፡ “አፍካውያን ቀደም ባሉ ገዜያት ለጸረ-ቅኝ አገዛዝ ባደረጉት ትግል የብርታት ብርሃንና የተስፋ ስንቅ ሆኖ ያገለገለቻውና ኢትዮጵያውያን በአንድነት የጻፉት ደማቁ የአድዋ ገድልን የሚያንጸባረቁ እንዲሁም በወቅቱ ከፍተኛ የመሪነት ሚና የነበራቸው አጼ ሚኒሊክን ጨምሮ በአጼ ቴዎድሮስ፣አጼ ዮሃንስ እና አጼ ኃይለ ስላሴ የተመሩ የተለያዩ ገድሎች የሚያሳዩ የስነጥበብ ውጤቶች ያሉበት ነው” ብሏል፡፡
ለአንድ ወር ያክል ክፍት የሚሆነው አውደ ርዕዩ፤ በቀን 100 የጥበብ አፍቃርያን እንደሚጎበኝም ነው የተገለጸው፡፡
ሰነ-ጥበብ -ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ትምህርት በሃሳብ ደረጃ ከተጸነሰ ዘመናት እንዳስቆጠረና ቀደም ባሉ ጊዜያት ተምረዋል በሚባሉ ሰዎች ልቦና ውስጥ የነበረ መሆኑን የታሪከ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
በንጉሥ ምኒልክ ዘመን ማብቂያና በዘውዲቱ የንግስና ዘመናት የነበሩ፤ ወደ ጣልያን እና ፈረንሳይ ተጉዘው ስዕል፣ ቀለም ቅብ እና ኪነ ሃውልት የመማር እድል ያገኙ ዘርይሁን ዶሚኒክ፣ ጌታቸው ዳፈርሳ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ አበበ ወ/ጊዮርጊስ እና አፈወርቅ ገ/እየሱስ የተባሉ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ቆይታቸው፤ “ጥንታዊውና ኢትዮጵያዊው የስነ-ስዕል ጥበብ በዘመናዊ የስነ ጥበብ ትምህርት መታገዝ አለበት” የሚል ከፍ ያለ ቅናት ይዘው የመጡ ሰዓሊያን እንደነበሩም ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያውያኖች ሰዓሊያን ከአውሮፓ መልስ ባለተሰጥኦ ህጻነትን መልምለው በፍላጎት ማስተማር ጀምረውም ነበር፡፡ በዚህም የያነው ወቅት “በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ-ጥበብ ትምህርት የተጀመረበት ጊዜ” ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
የስነ-ጥበብ ሰዎቹ በራሳቸው ተነሳሽት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም፤ የስነ-ጥበብ ትምህርት በተቋም ደረጃ እንዲደራጅ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ግን “አለፈለገ ሰላም” ናቸው፡፡
አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት
አለፈለገ ሰላም በአንጋፋው የአሜሪካ ቺካጎ የጥበብ አካዳሚ (Chicago Academy For the Arts) የተማሩና ለስድስት ወራት ያክል በስፔን፣ፈረንሳይ እና ጣልያን በመሳሰሉ ሀገራት በ20ኛው ክ/ዘመን በጣም ስመጥር በሚባሉ የስነ-ጥበብ ማዕከላት የሚገኙ ኦሪጂናል ስራዎች የጎበኙ ፣ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
አለፈለገ ሰላም፣ በአውሮፓ ምድር የተመለከቱትን ነገር ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሮባቸው በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በራሳቸው ተነሳሽነት፤ ትንሽ እርሾ ገንዘብ በማውጣትም ጭምር የዘመናዊ የስነ-ጥበብ ትምህርትን አስፈላጊነትን በተመለከተ ለንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ምክረሃሳብ አቅርበው፤ ምክረ-ሃሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ሃምሌ 16/1950 ዓ.ም በንጉሡ የልደት ቀን “አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት” ተመሰረተ፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ መስከረም 1951 ዓ.ም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ባለ ተሰጥኦ ልጆችን በመመልመል ፉም፣ ዊንዲ ኪንደር እና ሀርቨር ሳይለር በተባሉ የውጭ ሀገር መምህራን ማስተማር እንደጀመረም የሚታወስ ነው፡፡
ተቋሙ በጊዜ ሂደት እያደገ እንደመምጣቱ ሁላ “በአሳሳል ፈሊጥ ረገድ ከዓለም የስነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ጋር እኩል የሚራመዱ ትልቅ ለውጦች ማሳየት የቻለ” እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡
“ኤክስፕሬሽኒዝም፣ ኢምፕሬሽኒዝም እና ኢንድቪዥዋሊስቲክ” ትልቅ ተጽእኖ የፈጠሩና የዓለም ንግግር ያላቸው የአሳሳል ፈሊጦች ናቸው፡፡
የአለ አሁናዊ ሁኔታ
አለ የጥበብና ዲዛይን ት/ቤት አሁን ላይ በአምስት የመጀመርያ ዲግሪ ፕሮግራሞች (እስከ ፒ.ኤች.ዲ የሚደርስ ኢንተርዲሲፕሊነሪ ቪዥዋል አርት፣ ኪነ-ቅርጽ፣ የቀለም ቅብ፣ የህትመት ጥበባት እና ኢንዳስትሪያል ዲዛይን) እንዲሁም በሁለት የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች (ፊልም ፕሮዳክሽን እና ፋይን አርት) 200 ተማሪዎችን ተቀብሎ በሁሉም ደረጃዎች የማስተማር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ግቢውን የጎበኙ ሲሆን “ለመጀመሪያ ጊዜ በእንጠጦ ፓርክ ትልቅ የስነ-ጥበብ ማዕከል” አስገንብቷል፡፡
የስነ-ጥበብ ማእከሉ መከፈት ከማህበረስቡ ጋር ከመደበኛ የማስተማር ሂደቱ በተጨማሪ “ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ለመገናኘት እድል የሚፈጥር ነው” ተብሎለታል፡፡
አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት እንደ ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ እስክንድር ሞገስ፣ ዘርይሁን የትም ጌታ፣ ወርቁ ጎሹ፣ ወርቁ ማሞ፣ ወሰኔ ኮስሮፍ፣ ፕ/ር አቻምየለህ ደበላ፣ ጥበበ ተርፋ እንዲሁም ከዘመኑ ኤልያስ ስሜን የመሳሰሉ አንጋፋ የስነ-ጥበብ ሰዎችን ያፈራ ጥንታዊ የፓን አፍሪካኒዝም ጥበብ ት/ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡