አል ዐይን ኒውስ ከቻይና ሴንተራል ቴሌቪዥን (CCTV+) ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ
በስምምነቱ መሰረት ተቋማቱ ዘገባዎችን፣ ፎቶዎችን፣ ቪዲዮዎችንና የቀጥታ ስርጭቶችን ጨምሮ የተለያዩ ይዘቶች ይለዋወጣሉ
በሰራተኞች መካከል የልምድ ልውውጥ እና የጉብኝት መርሃ ግብርም የስምምነቱ አካል ናቸው
በአል ዐአይን ኒውስ እና በቻይና ሴንተራል ቴሌቪዥን (CCTV+) የቪዲዮ ዜና ኤጀንሲ መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈረመ።
ከአለም አቀፍ ሚዲያ ኢንቨስትመንቶች ኩባንያ (አይኤምአይ) ድርጅቶች አንዱ በሆነው “አል ዐይን ኒውስ” እና የቻይና ማዕከላዊ ቴሌቪዥን (CCTV+) በዜና ልውውጥ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የጋራ ትብብርን ለማሳደግ ዓላማ ያለው የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል።
የትብብር ስምምነቱ የተፈራመው በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው 11ኛው የዓለም ቪዲዮ ሚዲያ ፎረም (ቪ.ኤም.ኤፍ) ጎን ለጎን ሲሆን በጉባዔው ላይ የአል ዐይን ኒውስን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ሚዲያዎች ተወካዮች ተሳትፈውበታል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የአል ዐይን ኒውስ ዋና አዘጋጅ አህመድ አል-አላዊ እና የቻይና ሴንተራል ቴሌቪዥን (CCTV+) ዋና ስራ አስኪያጅ እና ዋና አዘጋጅ ጋኦ ዋይ ናቸው።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የሲሲቲቪ ምክትል ዋና ዳይሬክተር. ሊ ዢያ እና በአል አይን ኒውስ የዲጂታል ዘርፍ ዳይሬክተር ሃኒ ሲሞ ተገኝተዋል
የአል ዐይን ኒውስ ዋና አዘጋጅ አህመድ አል-አላዊ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ፤ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል የጋራ ስራ አስፈላጊነት ላይ የአል ዐይን ኒውስ ጠንካራ እምነት እንዳለው በመግለጽ፤ በተለይ ዲጂታል ሚዲያው ህብረተሰቡ ስለ አለም ያለውን ግንዛቤ በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ስላለው አፅንዖት ሰጥተነዋል ብለዋል።
የቻይና ሴንተራል ቴሌቪዥን (CCTV+) ዋና ስራ አስኪያጅ እና ዋና አዘጋጅ ጋኦ ዋይ በበኩላቸው፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የጋራ ትብብር መስፋፋት በደስታ መቀበላቸውን ገልጸው፤ CCTV+ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ለመመስረት ያለውን ፍላጎት አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአል ዐይን ኒውስ እና በ CCTV+ መካከል የጋራ ስራን ለማስፋት የሁለቱም ወገኖች ተመልካቾቻቸውን እና ተከታዮቻቸውን የሚጠቅም የበለጠ ትብብር ለማድረግ የጋራ ስራ መጀመሩንም አብስረዋል።
በተፈረመው ስምምነት መሰረት በሁለቱ የሚዲያ ተቋማት የተሰሩ የተለያዩ የዜና ይዘቶችን፣ ፎቶዎችን፣ የቪዲዮ ክሊፖችን እና የቀጥታ ስርጭቶችን ጨምሮ የተለያዩ ይዘቶች ይለዋወጣሉ።
በዚህ የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል "የቀጥታ መስመር" ይቋቋማል የተባለ ሲሆን፤ ይህም የጋራ ተጠቃሚነት የሚዲያ ትብብርን ለማምጣት ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
በተጨማሪም የልምድ ልውውጥ፣ የሁለቱ ሰራተኞች ተቋሞቹን መጎብኘት እንዲሁም በጋዜጠኝነት እና በቪዲዮ ፕሮዳክሽን ዘርፎች ላይ በጋራ መስራት የትብብሩ አካል ነው።