በፈረንጆቹ 2015 ስራውን የጀመረው አል ዐይን ኒውስ በ 5 ቋንቋዎች በአዲስ መልክ ስራ መጀመሩን አስታወቀ
በፈረንጆቹ 2015 ስራውን የጀመረው አል ዐይን ኒውስ በ 5 ቋንቋዎች በአዲስ መልክ ስራ መጀመሩን አስታወቀ
አል ዐይን ዜና አዲስ የዲጂታል ሚዲያውን ቅዳሜ በፈረንጆች ጥቅምት 24 በሁሉም የቋንቋ መድረኮቹ ፣ በዘርፉ ፈርቀዳጅ ለመሆን ባለው ቁርጠኝነት ላይ በመመርኮዝ ሙያዊ እና ተዓማኒ ይዘቶችን እጅግ በጣም ዘመናዊ በሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጀምሯል፡፡
አል ዐይን ዜና በአዲሱ እይታው ሁሉንም ዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያ ዓለም ውጤቶች በመጠቀም ይሰራል፡፡ ለዕይታዎ በሚማርክ መልኩ በአዲስ አቀራረብ ፣ በአዲስ የድረ ገጽ ዲዛይን (al-ain.com) ፣ በተጨማሪም በስማርትስልኮች እና በተለያዩ የዲጂታል ሚዲያ መተግበሪያዎች ላይ የሚነበቡ ፣ የሚደመጡና የሚታዩ ዘገባዎችን በአምስቱ ቋንቋዎች ማለትም በአረብኛ ፣ በፈረንሳይኛ ፣ በፋርስኛ ፣ በቱርክኛ እና በአማርኛ ይዞ ቀርቧል፡፡
አል ዐይን ዜና ለተከታዮቹ እና ለአንባቢዎቹ በአዲስ ዘመናዊ ዕይታ ፣ “አይንዎ በዓለም ላይ ነው” የሚል መፈክር አንግቦ ቀርቧል፡፡ የእድገት መጋረጃን በሰፊው ከፍቶ ዕይታዎን ለማርካት ለየት ባሉ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች መጥቷል፡፡ በተጨማሪም በርከት ያሉ ጥበብ የተሞላባቸው ቪዲዮዎችን ፣ እውነትን ፈትሸው የሚያቀርቡ ዘጋቢ ፊልሞችን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ሽፋን በመስጠት በርከት ያለ አንባቢ እና ተከታይ ጋር ለመድረስ ይሰራል፡፡
በአምስቱ ቋንቋዎች አል ዐይን ዜና በአዲስ አቀራረብ መጀመሩ ፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ዋና ከተሞች በስፋት መገኘቱን ከማስፋቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይም ካይሮ ፣ አዲስ አበባ ፣ ለንደን እና ዋሽንግተንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሙያው የተካኑ ዘጋቢዎችን አሰማርተናል፡፡ በዚህም ከምንሰራቸው ልዩ ቃለ-መጠይቆች በተጨማሪ ከእኛ ጋር በአስተሳሰባቸው የመጠቁ ታዋቂ ጸሓፍት እና አምደኞች በባህል ፣ በፖለቲካ እና በምጣኔ ሀብት ዙሪያ የሚጽፏቸውን አዳዲስ እና ወቅታዊ መጣጥፎችን እናቀርባለን፡፡
“ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን ኢንቬስትመንት ኩባንያ” በዚህ ዓመት መጀመሪያ በስሩ ካካተተው ወዲህ አል ዐይን ዜና የኩባንያውን አቅም የመጠቀም ፣ ከፍተኛ የአስተዳደርና የንግድ ሙያ የመቅሰም ፣ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ችሎታ እና የላቀ የቴክኒክ አቅም የማዳበር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ልምድ የመቅሰም አጋጣሚ ስላገኘ ተቋሙ የእድገትና የልማት ዕድሎችን ተጎናጽፏል፡፡
በዚህ ዝግጅት ላይ የአል ዐይን ዜና ዋና አዘጋጅ የሆኑት አህመድ ሰዒድ አል-ዑልዊ እንደተናገሩት በአምስቱ ቋንቋዎች የተጀመረው አዲስ አቀራረብ አል ዐይን ዜናን ታማኝ የዜና ምንጭ ያደርገዋል ፤ ይህም የዲጂታል ሚዲያ እድገት ገፀ ባህሪ ከሆነው የተለያዩ የማህበረሰቡ ክፍሎች የሐሳብ ልውውጥ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣም ነው፡፡
አል-ዑልዊ አክለውም “ይህ ለውጥ በዲጂታል ሚዲያ ዓለም ውስጥ ካሉ ለውጦች እና ፈጣን ቴክኖሎጂዎች ጋር የሚራመዱ መሳሪያዎች ባለቤት እንድንሆን የሚያደርገን ሲሆን ይህም በፈጠራ የታጀቡ ዜናዎችን፣ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ለማቅረብ ይጠቅመናል” ብለዋል፡፡
አል-ዑልዊ እንደገለጹት አል ዐይን ዜና ለመጪዎቹ ዓመታት አጓጊ ስትራቴጂዎችን ያዘጋጀ ሲሆን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎት የሚያሟላ ይዘት ለማቅረብ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን ፣ ዘመናዊ መተግበሪያዎችን ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂዎችን ፣ የቪዲዮ ዘገባዎችን እና የስማርትስልክ ዘገባዎችን በመጠቀም በአምስቱም ቋንቋዎች ያቀርባል፡፡
አል ዐይን ዜና በርካታ ተከታዮችን ያፈራ ሲሆን በፌስቡክ 3 ሚሊዮን 800 ሺህ ፣ በትዊተር ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በኢንስታግራም እና በዩ ቲዩብ ከ 786 ሺህ በላይ ተከታዮች አሉት፡፡ ከይዘት አንጻርም በልዩ አቀራረብ ከአረብኛ በተጨማሪ በፈረንሣይኛ ፣ በፋርስኛ ፣ በቱርክኛ እና በአማርኛ ያቀርባል፡፡
ስለ "አል ዐይን ዜና" በአጭሩ
በ 2015 የተቋቋመ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ሚዲያ መድረክ ነው፡፡ ከ“ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን ኢንቬስትመንት ፍሪ ዞን ኤልኤልሲ” ኩባንያ የንግድ ምልክቶች አንዱ ሲሆን (ዋና መስሪያ ቤቱ) በአቡ ዳቢ - የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይገኛል፡፡ በካይሮ ፣ በአዲስ አበባ እና በአሌክሳንድሪያም ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ዘጋቢዎቹ ሁሉንም ዓለምአቀፍ ክስተቶች እና የተለያዩ ሁነቶች በፍጥነት ይዘግባሉ፡፡
አል ዐይን ዜና ሁሉን አቀፍ ሽፋን የሚሰጥ እና የዓለም ክስተቶችን በወቅቱና በጊዜው ለተከታዮቹ የሚያደርስ ሲሆን ተዓማኒ ይዘቶችን በፍጥነት በዲጂታል መተግበሪያዎች አጣምሮ ያቀርባል፡፡ እንዲሁም ሪፖርቶችን ፣ ጥናቶችን እና ጥልቅ ትንታኔዎችን በምሁራን ፣ በፖለቲከኞች ፣በደራሲያን እና በተለያዩ ባለሙያዎች በማዳበር ያቀርባል፡፡