የሩሲያ ግስጋሴ ያሰጋው ኔቶ “የጦሩን ቁጥር ከ300 ሺህ በላይ ለማሳደግ” እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
የኔቶ ምላሽ ሰጪ ኃይል እስካሁን 40 ሺህ ወታደሮች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ
የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ማመልከቻዎችን እንዲያቀርቡ ያስገደደ መሆኑ ይታወቃል
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየተቀዳጀችው ያለው ወታደራዊ ድል ያሰጋው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጦሩን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ አስታወቁ፡፡
ዋና ጸሃፊው በቀጣይ ቀናት በማድሪድ ከሚካሄደው ስብሰባ በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “የኔቶን ኃይል እናጠናክረዋለን እንዲሁም የከፍተኛ ዝግጁነት ሀይላችንን ቁጥር ከ 300 ሺህ በላይ እናሳድጋለን" ብለዋል፡፡
የኔቶ ምላሽ ሰጪ ኃይል እስካሁን 40 ሺህ ወታደሮች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እናም የኔቶ የጦር ቁጥር ወደ ከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ እርምጃ ፑቲን በዩክሬን ምድር እያሳዩት ያለውን ወታደራዊ ግስጋሴና ቀጣይ ስጋት ከግምት ውስጥ ከግምት ያስገባ ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ፊንላንድ እና ስዊድን ወደ ምዕራባዊው ወታደራዊ ህብረት /ኔቶ/ ለመቀላቀል ማመልከቻዎችን እንዲያቀርቡ ያስገደደ ጉዳይ መሆኑም እሙን ነው፡፡
የኔቶ አባል ሀገራት የፊታችን እሮብ እና ሃሙስ በስፔን ማድሪድ ጉባኤቸውን ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸው የሚታወቅ ነው፡፡፡
ለስብሰባው የማድሪድ ሰዎች ከአሁኑ ጥብቅ የደህንነት ስራዎች እየሰሩ ሲሆን ከተማዋ ወታደራዊ መሪዎችን ለመቀበል ሽርጉድ እያለች እንደሆነም መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
ኔቶ በማድሪድ በሚያደርገው ጉባኤ ላይ የጥምረቱ አባል ለመሆን ጥያቄ ላቀረቡት ስዊድን እና ፊንላንድ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኔቶ እንደፈረንጆቹ ከ2010 ጀምሮ እንደ ስትራቴጂክ አጋሩ ሲያያት በነበረችው ሩሲያ ላይ የያዘው አቋም ይለውጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዋና ጸሃፊው ስቶልተንበርግም ቢሆኑ "በማድሪድ ውስጥ የምንስማማው በስትራቴጂካዊ ጽንሰ-ሀሳብ ውስጥ እንደዚያ እንደዚያ (እንደቀደመው) ሊሆን አይችልም" ነው ያሉት፡፡
“አጋሮቻችን ሁሉ፤ ሩሲያ በደህንነታችን፣ በእሴቶቻችን እና ህግ ላይ በተመሰረተው ዓለም አቀፍ ስርአት ላይ ቀጥተኛ ስጋት እንደ ፈጠረች በግልጽ እንደሚናገሩ እጠብቃለሁ” ሲሉም አክለዋል ዋና ጸሃፊው፡፡