አባላቱ ሩሲያ ማዕቀቦችን ተከትሎ እየናረ ከመጣው የነዳጅ ዋጋ ልትጠቀም የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች ስለመድፈን አበክረው እንደሚወያዩ ይጠበቃል
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ጉባኤያቸውን በሩሲያ ወርቅ ላይ ማዕቀብን በመጣል ጀመሩ፡፡
ለሶስት ቀናት ይቆያል የተባለው ጉባዔው በጀርመን መካሄድ ጀምሯል፡፡
የዓለማችን ሰባት ሀብታም ሀገሮች ስብስብ የሆነው የቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤያቸውን በጀርመን ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ መሪዎቹ ባቫሪያ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
መሪዎቹ ዛሬ እና ነገ በሚያደርጓቸው ውይይቶች የዓለምን ኢኮኖሚ እየፈተነ ባለው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር በገባችበት ይፋዊ ጦርነት ምክንያት በዓለም ላይ የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል፡፡
ምዕራባዊያንም በሩሲያ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን ቢጥሉም በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ጦርነት ከማቆም ይልቅ አጠናክራ ቀጥላለች። መጠነ ሰፊ ጉዳት እየደረሰም ይገኛል፡፡
ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ሩሲያን ለማሸነፍ የታቀደው ውጥን ፍሬ አለማፍራቱ እና ተጨማሪ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ እጅ ስር መውደቃቸው ምዕራባዊያኑን አሳስቧል፡፡
ሩሲያን በመቅጣት ዩክሬንን ማትረፍ በሚል ተይዞ የነበረው የምዕራባዊያን እቅድም ውጤት እያመጣ ባለመሆኑ ዩክሬን እና ሩሲያ አለመግባባታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ማሳሰብ ጀምረዋል፡፡
ለአብነትም ከሰሞኑ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሁለቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሲያሳስቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ደግሞ የሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
እነዚህ መሪዎች በተናጠል ያሉት ሀሳብ በቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ አቋም ሆኖ ሊወጣ እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤ ከሩሲያ ዩክሬን ጉዳይ በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ፣ በአየር ንበረት ለውጥ እና በቻይና ጉዳይ እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ካናዳ፣ ጣልያን እና ፈረንሳይ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ሲሆኑ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ አህጉራት መሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ይሄንን ጉባኤ ይሳተፋሉ፡፡