ኔቶ በቤላሩስ ድንበር አቅራቢያ ኑክሌር ማንቀሳቀሱን ተከትሎ ነው ሩሲያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው
ሩሲያ ለቤላሩስ የኑክሌር አረር ልታስታጥቅ መሆኑን ገለጸች፡፡
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገር የነበረችው ቤላሩስ ከዩክሬን ጋር ባለው ጦርነት ከሩሲያ ጎን ከቆሙ ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ናት፡፡
ከቤላሩስ ውጪ ሁሉም የቀድሞዎቹ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ከሩሲያ በተቃራኒ ወይም ከምዕራባዊያን ጎን ተሰልፈው የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን የምዕራባዊያንን ማዕቀብንም በማስፈጸም ላይ ናቸው፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ጦሩን በቤላሩስ ድንበሮች አቅራቢያ ማድረጉ ምቾት የነሳቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልክሳንደር ሉካሸንኮ ሞስኮን በመጎብነጠት ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያ አቻቸው ጋር በኔቶ ጦር ጉዳይ የተወያዩ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም ሩሲያ ለቤላሩስ ኑክሌር አረር ለማስታጠቅ መወሰኗን ገልጻለች፡፡
ሩሲያ ኢስካንዳር-ኤም የተሰኘውን ኑክሌር ተሸካሚ ሚሳኤል በጥቂት ወራት ውስጥ ለቤላሩስ እንደምታስታጥቅ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ሩሲ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ኔቶ የኑክሌር ሚሳኤሎችን በቤላሩስ ጎረቤት ሀገር በሆኑት ፖላንድ እና ሊቱንያ ድንበር አቅራቢያ ማንቀሳቀሱን ተከትሎ ነው፡፡