በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ ምትክ ማሊክ አካርን የሉዓላዊ ም/ቤት ም/ፕሬዝዳንት አድርገው መሾማቸው ተገልጿል
ጀነራል አልቡርሀን ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን ከስልጣን አነሱ።
በሱዳን ከ35 ቀን በፊት በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
የጦርነቱ ተፋላሚዎች በሳውዲ አረቢያ እና አሜሪካ አደራዳሪነት እየተደራደሩ እና ወደ ስምምነት እንደመጡ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ስምምነቱን ሲያከብሩ አልታዩም።
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ጀነራል አልቡርሀን ምክትላቸው የሆኑት እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች አዛዥ የነበሩት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን ከስልጣን መነሳታቸውን ገልጸዋል።
ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው ሄመቲ ከስልጣን እንደተነሱ ተገልጿል።
በጀነራል ሄመቲ ምክትልም ማሊክ አካርን መሾማቸው ተገልጿል።
ጀነራል ሄመቲ ከስልጣን ስለመነሳታቸው እስካሁን ያሉት ነገር እንደሌለም ተገልጿል።
በሱዳን ግጭት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ 20 ሺህ ገደማ ተፈናቃዮች መምጣታቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይኦኤም አስታውቋል።
በዚህ ጦርነት ምክንያትም እስካሁን ከ820 በላይ ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ የሱዳን ግጭት በሱዳናዊያን በሚመራ የሰላም ውይይት ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት እንዳለው መናገሩ ይታወሳል።
የሱዳን አለመረጋጋት ኢትዮጵያን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራትን መጉዳቱ እንደማይቀር የገለጸው ሚንስቴሩ ጉዳትን ለመቀነስ ሲባል 11 አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ መዋቀሩንም አስታውቋል።