የጅዳ ድርድር ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያተኩራል ተብሏል
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሳዑዲ አረቢያ የመጀመሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።
ሁለቱ ወገኖች “የቅድሚያ ስምምነት መርሆች” በጅዳ ተፈራርመዋል።
በጅዳ መግለጫ ሁለቱም ወገኖች ለሱዳን ሉዓላዊነትና አንድነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹ ሲሆን፣ የሱዳን ወዳጆች የሚያደርጉትን ጥረት በደስታ እንቀበላለን ማለታቸውን አል አረቢያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የጅዳ መግለጫ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ጥቃቶች እንደሚታቀቡ አረጋግጧል።
ስምምነቱ ኃይሎቹ በሱዳን ያሉ ሲቪሎች ያሉባቸውን አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡም ያስገድዳል።
በሱዳን የመንግስትና የግል ተቋማትን ለቆ ለመውጣት፣ የህክምና ባለሙያዎችን እና የህዝብ ተቋማትን መጠበቅ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መፍቀድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በድርድሩ ጦሩም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥያቄዎችን እና ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው ነበር ተብሏል።
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስምምነቱን በደስታ መቀበሉን ገልጾ፤ የጅዳ ድርድር በሁለቱ ወገኖች መካከል እስከ 10 ቀናት የሚቆይና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚያተኩር አስታውቋል።
"የደህንነት እርምጃዎቹ በአሜሪካ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደገፍ የተኩስ አቁም ቁጥጥር ዘዴን ያካትታል" ብሏል።
የአሜሪካ መንግስት በሰጠው መግለጫ ስምምነቱ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳልሆነ ተናግሯል።
የጂዳ ስምምነት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያመራ መደላደል እንደሆነም ተነግሯል።