የሱዳን ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የደቀናቸው ስጋቶች ምንድናቸው?
በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት አንድ ወር ሞልቶታል
ጦርነቱን ለማቆም ተፋላሚዎች ብዙ ስምምነቶችን ቢፈጽሙም ሁሉም ተጥሰዋል
በጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመቲ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ ነበር ጦርነት የተጀመረው፡፡
ይህ ጦርነት በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሱዳን ተስፋ ተጥሎበት የነበረውን በሲቪል የሚመራ መንግስት የመመስረት ጉዳይን ማምከኑ ተገልጿል፡፡
ጦርነቱ ስልጣንን ለመቆጣጠር በሚል መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያንን ህይወት ሲቀጥፍ ለተለያዩ ስራዎች ወደ ሱዳን ገብተው የነበሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ለቀው እንዲወጡም አስገድዷል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ጥልቅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ባላት ሱዳን የተጀመረው ይህ ጦርነት ወዴት ያመራ ይሆን? በለኢትዮጵያ ላይስ ምን ጉዳት ሊኖረው ይችላል?
አል ዐይን አማርኛ በጉዳዩ ዙሪያ የሰላምና ደህንነት ምሁራንን አናግሯል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከሆነ የሱዳን ጦርነት እልባት ካላገኘ እና ከቀጠለ ኢትዮጵያን ወደ ተባባሰ ችግሮች ሊያስገባት ይችላል፡፡
ምስራቅ አፍሪካ የምዕራባዊያን፣ሩቅ ምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስብስብ ፍላጎት ያለበት አካባቢ በመሆኑ የሱዳን ጦርነት ቅርጹን እየቀያየረ ሊቀጥል ይችላልም ብለዋል፡፡
ሱዳን ኢትዮጵያን ጨምሮ የቻድ፣ ሊቢያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ግብጽ ጋር ትዋሰናለች ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ጦርነቱ በነዚህ ሀገራት ላይ ሁሉ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም ሲሉም አክለዋል፡፡
ከግብጽ በስተቀር ሌሎቹ የሱዳን ጎረቤት ሀገራት የሰላም ችግር ያለባቸው መሆኑ በነዚህ ሀገራት ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲሰፋ፣ የታጠቁ እና ሽብርተኛ ሀይሎች የበለጠ ለመደራጀት እድል እንዲያገኙ የማድረግ እድልም እንዳለው ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዋነኛ ተጎጂ ሆናለች የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል ስደተኞችን በመቀበል፣ ተጨማሪ የኢኮኖሚ እና ሌሎች ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ ማድረሳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የሱዳን ተፋላሚዎች በተደጋጋሚ ወደ ስምምነት ቢመጡም ስምምነቱቹ በዛው ልክ መጣሳቸው እየጠኬደበት ያለው መንገድ ትክክል ላለመሆኑ ማሳያ እንደሆነም አክለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ ይህ ጦርነት ከተባባሰ እና መቋጫ ካላገኘ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነትን ሊያበላሽ ወደሚችል መንግድ ሊቀየር ይችላልም ብለዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ ድንበር ጉዳይ እልባት አለመሰጠቱ እና ጦርነቱ መቀጠሉ ጉዳዩ እንዲወሳሰብ ማድረግ፣ በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት እንዲገባት በማድረግ ላልተገባ የሰላም እና የደህንነት ወጪ ሊዳርጋት እንደሚችልም ዶክተር ሳሙኤል ነግረውናል፡፡
ከዚያ በተጨማሪም በስደተኞች ስም የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ተልዕኮዎችን የያዙ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እና አሸባሪዎች የበለጠ እንዲደራጁ እድል ሊያገኙም ይችላሉ ብለዋል፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ በድርቅ፣ በጦርነት፣ በኑሮ ውድነት እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነ ላለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጨማሪ ስጋት ሊሆን እንደሚችልም አክለዋል፡፡
የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በተደጋጋሚ ወደ ስምምነት እየመጡ እና በዛው ልክ ስምምነቶችን አለማክበራቸው ጦርነቱ በቅርቡ ላይቆም እንደሚችል ማሳያ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶክተር ሳሙኤል በሱዳን ሰላም አስከባሪ እስከመግባት የሚደርሱ ውሳኔዎች ሊደርሱ ይችላሉም ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ተባብሶ የሱዳን ጉዳይ ከአቅም በላይ ከሆነ እና ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲገባ ከጸጥታው ምክር ቤት እስከ አፍሪካ ህብረት ድረስ ሊወሰን ስለሚችል እዚህ ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ውሳኔዎች እንዳይወሰኑ ጉዳዩን በቅርበት መከታተል ይገባል ተብሏል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ እና በሚገባ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማገዝ ለሱዳን ጦርነት እልባት የተሻለው መፍትሔ እንደሚሆንም ዶክተር ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሱዳንን መርዳት የምትችልበት አቋም ላይ አለመሆኗን የተናገሩት ደግሞ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አበበ ይርጋ ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት ከሆነ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ህዝብ ትስስሩ ጥልቅ መሆኑን ተከትሎ የተሻለ ደህንነት ፍለጋ የሚመጡ ዜጎች ቁጥር ይጨምራል፡፡
ይህን ተከትሎም ጦርነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማበላሸት ጀምሮ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የጀመረችውን ድርድር በድል እንዳታጠናቅቅ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በራሷ ሀብት እየገነባች ቢሆንም ግብጽ እና ሌሎች አካላት የሚያቀርቧቸውን መርህ አልባ ሀሳቦችን ድል በማድረግ የዲፕሎማሲ የበላይነት መያዝ የምትችለው ድርድሩ እስከመጨረሻው ሲቀጥል መሆኑንም ምምህር አበበ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሱዳን ሰላም በነበረችበት ወቅት ከፖርት ሱዳን እና ከሌሎች የንግድ መሰረተ ልማቶች ስታገኛቸው የነበሩ ጥቅሞችን በጦርነቱ ምክንያት እንደምታጣም ተገልጿል፡፡
ሰላም በራቃቸው እና የሽብርተኞች መንቀሳቀሻ በሆኑት የሱዳን ጎረቤት ሀገራት ውስጥ የነበሩ ችግሮች የበለጠ ለኢትዮጵያ ቅርብ እንዲሆኑ እና ኢትዮጵያን የበለጠ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያጋልጣት ይሆናልም ብለዋል፡፡
በሱዳን ጦርነት ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስም ኢትጵያ ለሱዳን መረጋጋት ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በአማራ ክልል እና ሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎች ላሉ የጸጥታ ችግሮች ምላሽ መስጠት፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ጥብቅ የጸጽታ እና ቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም መምህር አበበ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው መግለጫ የሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያን መጉዳቱ እንደማይቀር ገልጾ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችል 11 አባላት ያሉት ብሐየራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን መግለጹ ይታወሳል፡፡