አለርት ማዕከል “ለአፍሪካውያን በቴሌ-ኮንፈረንስ የህክምና አገልግሎት” የሚሰጥበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገለጸ
ማዕከሉ“በአፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማእከል ሆኖ ለመውጣትና ያለውን ስም ለማስቀጠል” እየሰራ ነውም ተብለዋል
አለርት በየዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት “የአፍሪካ ማሰልጠኛ ማዕከል” የሚል እውቅና የተሰጠው ተቋም መሆኑ ይታወቃል
አለርት ማዕከል (የመላው አፍሪካ ስጋ ደዌ፣ቲቢ መከላከያና ትምህርት መስጫ ማዕክል ) ከቆዳና ተያያዥ ህመሞች በተያያዘ በአፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማእከል ሆኖ ለመውጣት እየሰራ መሆኑ የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እስማኤል ሸምሰዲን ገለጹ፡፡
አለርት ማዕከል ሲቋቋም ከቆዳ እና ስጋ ደዌ ህመም ጋር ተያይዞ ማከምያ፣ ማስተማርያና የማገገሚያ አገልገሎት ለመስጠት በሚል ሲሆን አሁን ላይ የቲቢን ጨምሮ ሶስተኛ ደረጃ የህክምና አገልግሎቶች በመስጠት ላይ የሚገኝ መዕከል ነው፡፡
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እስማኤል ሸምሰዲን ማዕከሉ ሲጀመር አፍሪካን ያማከለ ግዙፍ ራእይ ይዞ የተነሳ መሆኑንና የአህጉሪቱ ባለሙያዎች ማሰልጣኛ ሆኖ ለረዥም ጊዜ መዝለቁን ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
ከቆዳ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ማዕከሉ ትልቅ ልምድ አለው ያሉት ዶ/ር እስማኤል፤ ካለው ልምድ የተነሳ ከተለያዩ ሀገራት ማለትም “ከአፍሪካ፣ኦሺንያ እና ደቡብ ኤስያ የሚመጡ የህክምና ባለሙዎች ስልጠና የሚያገኙበት”ና ጥልቅ ጥናትና ምርምሮች የሚካሄድበት ተቋም መሆኑንም ገለጸዋል፡፡
“ከቆዳና ተያያዝ ህመሞች ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማእከል ሆኖ ለመውጣትና ያለውን ስም ለማስቀጠል እየሰራ ነው” ብለዋል የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እስማኤል ፡፡
ከጉዳት ጋር በተያያዙ ህክምናዎች እንዲሁም በአከባብያዊ በሽታዎች (Tropical diseases) ላይ ማዕከሉን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጭምር ተናግሯል፡፡
አለርት በቆዳ ሳይወሰን በስጋ ደዌ እና ዐይን ህክምና የረዥም ጊዜ የዳበረ ልምድ እንዳለውም አንስተዋል ዶ/ር አስማኤል፡፡
አለርት በተለይም በቆዳ ህክምና ካለው ልመድ አንጻር “ሌላ ቦታ ያሉ ሀኪሞች ምስል አንስተው በሚያጋሩት ምስሎች ተንተርሶ በቴሌ-ኮንፈረንስ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል”ም ብሏል፡፡
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት/World Health Organization/ አለርትን “የአፍሪካ ማሰልጠኛ ማዕከል” የሚል እውቅና እንደሰጠውም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግሯል፡፡
ዶ/ር እስማኤል አለርት በሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር የተነደፈውን የአምስት አመት ሰትራቴጂክ እቅድ ብሎም ተቋሙ ያስቀመጠውን መርሀ-ግብር እውን ለማድረግ እየተጋ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
አለርት ሰፊው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የማድረግ ራእዩ እውን ኢንዲሆን “ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት፣ የጥናትና ምርምሮች ጥራትና ብዛት ከፍ ከማድረግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ግንኙነት ከማደስ አንጻር የሚሰራ ይሆናል”ም ብሏል፡፡
አለርት ማዕከል በሆስፒታል ደረጃ በርካታ ታካሚዎችን ይዞ አገልገሎት በመስጠት በኩል በሀገሪቱ አንደኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡