አዲስ አበባ ከ1 ሚሊዮን ለሚልቁ ነዋሪዎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ልትሰጥ ነው
ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ከ18 ዓመት በላይ ያሉ ነዋሪዎች ክትባቱን እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው
ክትባቱ ከ35 ዓመት እድሜ በላይ ላሉ ዜጎች በነጻ እንደሚሰጥ ተገልጿል
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለ1 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሮና ቫይረስ ከትባት ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ የኮቪድ 19 ወረርሸኝ ያለበት የስርጭት ሁኔታ እና የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነትን በተመለከተ መግለጫ ተሰጥተዋል ።
ሃላፊው በመግለጫቸው እንደተናገሩት ባለፉት አራት ሳምንታት በከተማዋ በኮቪድ 19 ወረርሸኝ የመያዝ፣ በጽኑ የመታመምና የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማእበል መከሰቱን የሚያመላክት ሁኔታ መታየቱንም ነው ዶ/ር ዮሐንስ ያመለከቱት።
የቫይረሱን ስርጭት ከመቆጣጠር ጎን ለጎን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ሆኖ ተጓዳኝ ሕመም ላለባቸውና ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት በሁሉም የመንግስት ጤና ጣቢዎች በነጻ መስጠት መጀመሩንም ገልጸዋል ።
ዶ/ር ዮሐንስ ቀደም ሲል ክትባቱን ያላገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለመከተብ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ትግበራ መገባቱንም ተናግረዋል።
በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት ተጋላጭ ለሆኑ የተለዩ የ105 የመንግሥትና የግል ተቋማት ሠራተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ሀላፊው ገልጸዋል።
በከተማዋ ለክትባት ከተለዩት ተቋማት መካከል የትራንስፖርት ዘርፍ፣ የግልና የመንግሥት ባንኮች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች እና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱ እንደሚሰጣቸው የጠቆሙት ኃላፊው ወረርሽኙን ለመከላከል ክትባቱ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ሕብረተሰቡ ማስክ በማድረግ፣ የእጅ ንጽህናና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ራሱን እንዲከላከልም አሳስበዋል።