ኢትዮጵያ ‘ዴልታ’ የተሰኘውን አዲሱን የኮሮና ቫይረስ ዝርያ እስከሁን ለመመርመር አልቻለችም ተባለ
ኬሚካሉን ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ያስታወቀው ጤና ሚኒስቴር በቅርቡ መመርመር እንደሚጀምር አስታውቋል
ይህ የሆነው ዝርያውን ለመመርመር የሚያስፈልገው ኬሚካል ወይም ‘ሪኤጀንት’ ሃገር ውስጥ አለመኖሩን ተከትሎ ነው
በኢትዮጵያ ‘ዴልታ’ የተሰኘውን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መመርመር አለመጀመሩን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እስካሁን ‘ዴልታ’ የተሰኘውን አዲስ ልውጥ የኮቪድ ዝርያ መመርመር አልጀመረችም።
እንደ ዶ/ር ሊያ ገለጻ ምርመራው እስካሁን ያልተጀመረው ዝርያውን ለመመርመር የሚያስፈልገው ኬሚካል ወይም ‘ሪኤጀንት እስካሁን ወደ አገር ውስጥ የለም።
ይሁንና “ኬሚካሉን ከውጭ አገር ለማስገባት በሂደት ላይ በመሆናችን በቅርቡ ምርመራው ይጀመራል” ብለዋል ዶ/ር ሊያ።
የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር በአዲስ አበባ 59 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጪ 20 በመቶ ናቸው።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሊያ “ወደ ጽኑ ህክምና የሚገቡ ዜጎች፣በቫይረሱ የሚያዙ እና ህይወታቸው የሚያልፉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ“ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።
ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥም ወደ ጽኑ ህክምና የሚገቡ ዜጎች በ2.5 በመቶ ሲያሻቅብ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር ከ2.8 በመቶ ወደ 7.4 በመቶ ከፍ ሲል ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ቁጥር ደግም ከ13 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማሻቀቡ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።