የደቦ ፍርድ የተፈጸመበት ግለሰብ የእሳት አደጋ ለማጥፋት በሚል ለእርዳት የመጣ ነው ተብሏል
በሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀሪያ ከአንድ ዓመት በፊት በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው ካቢሌ ግዛት የእሳት አደጋ ተከስቶ 90 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ቆስለው ነበር፡፡
ይህን የእሳት አደጋ ለመከላከል በሚል የ38 ዓመቱ ጃሜል ቤን እስማኤል የተባለ ግለሰብ ከሚኖርበት ሚላኒያና ከሚባለው የአልጀሪያ ከተማ ተነስቶ 322 ኪሎ ሜትር ተጉዞ እሳት ወአደጋው ወደ ተከሰተበት ቦታ ይደርሳል፡፡
ይሁንና የአካባቢው ማህበረሰብ ሊረዳቸው የመጣውን ግለሰብ ለእሳት አደጋው መከሰት ምክንያት አንተ ነህ በሚል ከነ ህይወቱ በእሳት አቃጥለው እንዲሞት እንዳደረጉት የአልጀሪያ ፍትህ ቢሮ ገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ፍርድ ቤትም በዚህ የደቦ ፍርድ ተሰማርተዋል ያላቸውን 49 ተጠርጣሪዎች በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ቢቢሱ ዘግቧል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጥፋተኛ በተባሉት ሰዎች ላይ ላይፈጸም እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊቀየር ይችላል ተብሏል፡፡
እነዚህ 49 ተጠርጣሪዎች ሊረዳቸው ከሌላ አካባቢ የመጣውን አልጀሪያዊ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የገደሉበትን የሚሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተዘዋውሮ በወቅቱ ብዙዎችን አስቆጥቶም ነበር፡፡
የሟች አባት የሆኑት ኑረዲን እስማኤል “ልጄ እሳቱ ወደ ተከሰተበት ቦት ያመራው አካባቢውን ስለሚወደው ለእርዳታ ነበር ይሁንና የአካባቢው ወጣቶች ግን ከነነፍሱ አቃጥለው ገድለውታል” ሲሉ በወቅቱ ለብዙሃን መገናኛዎች ተናግረዋል፡፡
የሟች ወንድም በበኩሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የወንድሙን አገዳደል የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል እንዲሰርዙት ጠይቆ የነበረ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ አናታቸው የልጇን መሞት እንጂ እንዴት እንደሞተ ስለማታውቅ እንደሆነ ማሳሰቡን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡