ፖለቲካ
በናይጄሪያ ዛምፋራ ግዛት ታጣቂዎች ከ100 በላይ ሰዎችን አገቱ
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ታጣቂዎች ሰዎችን እየጠለፉ ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ ተስፋፍቷል ተብሏል
የሀገሪቱ መንግስት ታጣቂዎች ከሰራዊቱ የሚደርስባቸውን የአየር ጥቃት ለመከላከል "የሰው ጋሻ" አድርገው እየተጠቀሙ ነው ብሏል
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ ዛምፋራ ግዛት ታጣቂዎች አራት መንደሮችን በመውረር ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች አፍነው ወስደዋል ተብሏል።
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ወንጀለኞች ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ሰዎችን ከመንደር፣ ከአውራ ጎዳናዎች እና ከእርሻ ቦታዎች እየጠለፉ ዘመዶቻቸው ማስለቀቂያ እንዲከፍሉ በመጠየቅ ጠለፋ ተስፋፍቷል ነው የተባለው።
በዛምፋራ ዙርሚ አካባቢ በሚገኘው የካንዋ መንደር ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ሮይተርስ የአካባቢውን ማስታወቂያ ኮሚሽነርና ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል። ሌሎች 37 ሰዎች በአብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት መታገታቸውንም እንዲሁ።
ሽፍቶቹ ለሁለት ተከፍለው በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከ14 እስከ 16 አመት እድሜ ያላቸው ህጻናትን እና ሴቶችን እያገቱ ነው ተብሏል።
ማራዱን በተባለ አካባቢም ቢያንስ 38 ሰዎች በእርሻቸው ላይ ሲሰሩ ታግተዋል ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳደር ታጣቂዎቹ አፍነው የወሰዷየውን ሰዎች ከሰራዊቱ የሚደርስባቸውን የአየር ጥቃት ለመከላከል "የሰው ጋሻ" አድርገው እየተጠቀሙ ነው ሲል ወቅሷል።