ጠንካራ ተከላካይ ቡድን በመስራት የሚታወቁት ካርሎስ ኬሮዥ በሶስቱ አናብስት ኮከብ ተጫዋቾች ተፈትነው ተሸንፈዋል
በአለም ዋንጫው የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ እንግሊዝ በኢራን ላይ 6 ጎሎችን አስቆጥራ አሸንፋለች።
በካሊፋ አለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በጀርመን ቡንደስሊጋ ለዶርትሙንድ የሚጫወተው ጁድ ቢሊንግሃም በ35ኛው ደቂቃ ቀዳሚዋን ጎል ለእንግሊዝ አስቆጥሯል።
የአርሰናሉ ቡካዮ ሳካ በ43ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎልም ሶስቱን አናብስት አነቃቅቷል።
ራሂም ስተርሊንግ ደግሞ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠ ተጨማሪ ስአት ሀገሩ 3 ለ 0 እየመራች ለእረፍት እንድትወጣ አድርጓል።
ሳካ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ አራተኛውን ጎል በ62ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ተስፈኛ ተጫዋችነቱን አሳይቷል።
የፐርሺያ ኮከቦቹ በፖርቶው ኮከብ ሜህዲ ታራሚ 65ኛ ደቂቃ ጎል ወደ ድል ለመመለስ ጥረት አድርገው ነበር።
ይሁን እንጂ የማንቸስተር ዩናይትዱ ማርከስ ራሽፎርድ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ 5ኛውን ጎል አስቆጥሮ ተስፋቸውን አጨልሞታል።
ጃክ ግሪሊሽ በ90ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎልም ከ56 አመት በኋላ የአለም ዋንጫውን ለማንሳት ለጎጉት ጋሬዝ ሳውዝጌት ድንቅ ጅማሮ አድርጎለታል።
ኢራን በተጨማሪ ስአት ያገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ማህዲ ታራሚ አስቆጥሮ ጨዋታው 6 ለ 2 ተጠናቋል።
ስምንት ጎሎች የተስተናገደበት ጨዋታ የፐርሺያ ኮከቦቹ ደካማ መከላከል ያሳዩበት ነበር።
መከላከልን መሰረት ያደረገ ቡድን በመስራት የሚታወቁት ካርሎስ ኬሮዥም የእንግሊዝ የፊት መስመርን መቋቋም የሚችል ቡድንን መስራት አልቻሉም፤ ስሜታቸውንም መቆጣጠር ሲሳናቸው ታይቷል።