ዩክሬን በኃይል እጥረት ምክንያት ዜጎቿ እንዲሰደዱ ምክረ ሀሳብ አቀረበች
ሩሲያ በሰነዘረችው ጥቃት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከኤሌክትሪክ ውጪ ሆነዋል ተብሏል
ሩሲያ በሰነዘረችው ጥቃት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከኤሌክትሪክ ውጪ ሆነዋል ተብሏል
ዩክሬን በኃይል እጥረት ምክንያት ዜጎቿ እንዲሰደዱ ምክረ ሀሳብ አቀረበች፡፡
ባሳለፍነው የካቲት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዘጠኝ ወራት የሞላው ሲሆን ጦርነቱ ይቆማል ቢባልም በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
ከነዚህ ክስተቶች መካከልም ሩሲያ ራት የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ራሷ በህዝበ ውሳኔ የጠቀለለች ሲሆን ኬርሰን ግዛት መልሳ በዩክሬን ጦር ተይዛለች፡፡
ሁለቱ አካላት ጦርነቱን በውይይት ይቋጫሉ ቢባልም ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ወደ ድርድር ሊመጡ ያልቻሉ ሲሆን ምዕራባዊያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የዩክሬን ሀይል አቅራቢ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ማክሲም ቲምቸንኮ ዩክሬናዊያን ከቻሉ ቢሰደዱ የተሻለ ነው ሲሉ ምክረ ሀሳብ አስቀምጠዋል፡፡
ሩሲያ ከሰሞኑ ባደረሰችው የሚሳኤል ጥቃት የሀገሪቱ 50 በመቶ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መውደሙ ሲገለጽ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከመብራት አገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዩክሬናዊያን የሀይል እጥረት እንደ ሀገር የገጠመ በመሆኑ ዜጎች ለጥቂት ወራት ከመሰደድ ጀምሮ ሌሎች ሀይል መቆጠቢያ መንገዶችን እንዲከተሉም ምክር ቀርቦላቸዋል፡፡
ሀይል በተቆጠበ ቁጥር ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት የቆሰሉ ወታደሮች በቀላሉ እንዲታከሙ እድል ስለሚያገኙ በሀይል ቁጠባ እንዲተባበሩም ስራ አአስኪያጁ አክለዋል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት የሩሲያ በሀይል መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረው የሰሞኑ ጥቃት ዩክሬን የሰላም ድርድሩን አልቀበልም ማለቷን ተከትሎ የተደረገ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የዩክሬን መንግስት አክሎም ዜጎች እንደ ምግብ ማብሰያ የመሳሰሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ቁሳቁሶችን እንዳይጠቀሙ ያሳሰበ ሲሆን የሩሲያ ጥቃት በዚሁ ከቀጠለ ዩክሬን ሙሉ ለሙሉ ከሀይል ውጪ ልትሆን ስለምትችል ተዘጋጁ ሲሉም አሳስቧል፡፡