በአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪዎች እነማን ናቸው?
ስድስተኛ የአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፎውን የሚያደርገው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በጀርመንስ አዲስ ክብረወሰን ያስመዘግብ ይሆን?
የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ ምሽት አዘጋጇ ጀርመን ከስኮትላንድ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል
ከ64 አመት በፊት ጅማሮውን ያደረገውና ተጠባቂው የአውሮፓ ዋንጫ በየአመቱ የተለያዩ ክብረወሰኖች ተሰብረውበታል።
17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ በሶስት ጊዜ ሻምፒዮኗ ጀርመን አስተናጋጅነት ሲጀመርም የቀደሙት ሪከርዶች እንደሚሻሻሉ ይጠበቃል።
በውድድሩ ታሪክ የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ ክብርን የያዘው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በጀርመን ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
የአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ
ለሳኡዲው አልናስር እየተጫወተ የሚገኘው ሮናልዶ በውድድሩ 14 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
ፖርቹጋል በ2004 ባዘጋጀችው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ በአለማቀፍ ጨዋታ የመጀመሪያ ጎሉን ያስቆጠረው በግሪክ ላይ ያስቆጠረው ሮናልዶ፥ በዚያው ውድድር ኔዘርላንድስ ላይ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ሮናልዶ ከ2004 ጀምሮ እስከ 2020 ድረስ በአምስት የአውሮፓ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍና ቢያንስ አንድ ጎል በማስቆጠርም ኮከብ ተጫዋችነቱን አረጋግጧል።
ፖርቹጋል በ2016 አዘጋጇን ፈረንሳይ አሸንፋ ዋንጫ ባነሳችበት ውድድርም ሶስት ጎሎችን ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።
ጣሊያን ሻምፒዮን በሆነችበት የ2020 የአውሮፓ ዋንጫም አምስት ጎሎችን በማስቆጠር የወርቅ ኳስ መሸለሙ አይዘነጋም።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሌላ አዲስ ክብረወሰን በጀርመን ከፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ጋር ይገኛል።
ከአንድ ጊዜ በላይ ሀትሪክ የሰራው ተጫዋች ማን ነው?
ከሮናልዶ በመቀጠል በአውሮፓ ዋንጫ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረው ፈረንሳዊው ሚሸል ፕላቲኒ ነው።
ፕላቲኒ ሀገሩ በ1984 ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓን ዋንጫ ስታነሳ ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሯል።
በቤልጂየም እና የያኔዋ ዩጎዝላቪያ ላይ ሶስት ሶስት ጎሎችን በማስቆጠርም በአንድ የውድድር አመት ከአንድ ጊዜ በላይ ሃትሪክ በመስራት የያዘው ክብረወሰን እስካሁን አልተሰበረም።
አለን ሽረር እና አንቶኒዮ ግሪዝማን በእኩል ሰባት ጎሎች ከሮናልዶ እና ፕላቲኒ ቀጥለው የበርካታ ጎል አስቆጣሪዎቹን ደረጃ ይዘዋል።
በርካታ ጎሎች የተቆጠሩባቸው ጨዋታዎች
በውድድሩ ታሪክ በአምስት የጎል ልዩነት የተጠናቀቁት አምስት ጨዋታዎች ናቸው። ኔዘርላንድስ በ2000 ዩጎዝላቪያን 6 ለ 1 ያሸነፈችበት ጨዋታ በርካታ ጎሎች የተቆጠሩበት ነው።
ፈረንሳይ 5 – 0 ቤልጂየም (1984)
ዴንማርክ 5 – 0 ዩጎዝላቪያ (1984)
ስዊድን 5 – 0 ቡልጋሪያ (2004)
ስሎቫኪያ 0 – 5 ስፔን (2020)