ሊዮኔል ሜሲ ስለ ቀጣይ እግር ኳስ ክለብ ቆይታውና ስለ እግር ኳስ ጉዞው ማብቂያ ጊዜ ምን አለ?
ሜሲ “እግር ኳስን እንደማልጫወት ሳስበውም ልቤ በሀዘን ይሞላል፤ ነገር ግን ግዜው የደረሰ ይመስላል” ብሏል
አረጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ከኳስ አለም እራሱን መቼ ሊያል ይችላል በሚለው ዙሪያ አስተያየት ሰጥቷል
አረጀንቲናዊው የእግርኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የአሜሪካው ኢንተር ሚያሚ የመጨረሻ ክለቡ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
ከእግር ኳስ እራሴን ሙሉ ለሙሉ ለማግለል ዝግጁ አይደለሁም ያለው ሜሲ በተለያዩ የእግር ኳስ ቡድኖች ያደረገው ቆይታ በኢንተር ሚያሚ ሊቋጭ እንደሚችል ለኢኤስፒኤን ተናግሯል።
“እግር ኳስን መጫዎት በጣም እወዳላሁ ከዚህ በኅላ እንደማለጫወት ሳስበውም ልቤ በሀዘን ይሞላል ነገር ግን ግዜው የደረሰ ይመስላል” ነው ያለው።
የአለም የእግርኳስ ኮከብ ሜሲ አሁንም ልምምዶችን መስራት እና እግር ኳስ መጫወት እንደሚያስደስተው ገልጾ በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ተናግሯል።
የ8 ባላንዶሮች አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ረጅም የእግር ኳስ ህይወቱን ባሳለፈበት የስፔኑ ባርሴሎና 4 የሻምፒዎንስ ሊግ እና 10 የላሊጋ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
በባርሴሎና በነበረው ቆይታ 672 ጎሎችን በማስቆጠር የክለቡ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ክብርንም ተቀዳጅቷል።
ከፈረንሳዩ ፒኤስ ጂ ወደ አሜሪካው ሜጄር ሊግ ሶከር ኢንተር ሚያሚ የተዘዋወረው ሜሲ የሊጉ መሪ ለሆነው ክለቡ በዘንድሮው የውድድር አመት ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን እና 13 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።
ሜሲ በእግር ኳስ ዘመኑ የምንግዜም ምኞቱ የነበረውን የአለም ዋንጫ ድል በ2022 ማሳካት ችሏል።
በዘንድሮው ኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ተጫዋቹ በ2021 ሀገሩ ያሳካችውን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ድጋሚ ለማንሳት እጫወታለሁ ሲል ተናግሯል።
በባለፈው አመት የአሜሪካውን ክለብ የተቀላቀለው ሊዮኔል ሜሲ ኮንትራቱ በሚቀጥለው አመት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ኢንተር ሚያሚ የመጨረሻው ክለቡ እንደሆነ ቢገልጽም ከክለቡጋር ኮንትራቱን አራዝሞ የመቆየት ፍላጎት እንዳለው በግልጽ አልተናገረም።