በመሳሪያ የታገዘ የተቃውሞ እንቅስቃሴን በመስጋት ሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው
የሀገሪቱ ካፒቶል ሂል ዙሪያ በአጥር እና በወታደሮች ተከቧል
የትራምፕ ደጋፊዎች ተከታዮቻቸው የጦር መሳሪያ ይዘው ሰልፍ እንዲወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸው ተሰምቷል
በዋሺንግተን የሚገኘው የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ-ካፒቶል ሂል ባልተለመደ መልኩ ዙሪያውን በአጥር ታጥሮ በወታደሮችም ተከቧል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከ 3 ቀናት በኋላ በሚካሔደው የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት ላይ ከቀናት በፊት ታህሣሥ 28 የተከሰተውን አይነት አመጽ እንዳይፈጠር በመስጋት ነው፡፡
የአሜሪካ የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በሁሉም የዐሜሪካ ግዛቶች የትራምፕ ደጋፊዎች በጦር መሳሪያ የተጋዘ አመጽ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ባይደን በዓለ ሲመት ድረስ ሊቆይ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን አመጽ ለመከላከል ሁሉም (50) የአሜሪካ ግዛቶች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
ዋናው የካፒቶል ሂል ከወዲሁ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ሲሆን ፣ ወደ ካፒቶሉ የሚያመሩ በርካታ መንገዶች በኮንክሪቶች እና በብረት አጥሮች ተዘግተዋል፡፡
ለበዓለ ሲመት ብዙውን ጊዜ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች የሚሞላው ብሔራዊ ሞል በሚስጥር አገልግሎት (ሴክሬት ሰርቭስ) ጥያቄ መሠረት ተዘግቷል፡፡ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ፣ አስቀድሞም የባይደን ቡድን አሜሪካውያን ለበዓለ ሲመቱ ወደ ዋሺንግተን እንዳያቀኑ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎች እና አክራሪ ቀኝ ዘመሞች ዛሬ ዕሁድ ጥር 09 ቀን 2013 ዓ.ም ተከታዮቻቸው ከነትጥቃቸው ሰልፍ እንዲወጡ በተለያዩ የትስስር ገጾቻቸው ጥሪ ማስተላለፋቸው የተሰማ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡
የተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች የጸጥታ ኃይላቸውን በተጠንቀቅ ከማሰለፍ ባለፈ ሌሎች እርምጃዎችንም በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡ ሜሪላንድ ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ዩታህ ግዛቶች ከወዲሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡
ካሊፎርኒያ ፣ ፔንሲልቫኒያ ፣ ሚሺጋን ፣ ቨርጂኒያ ፣ ዋሺንግተን እና ዊስኮንሲን ደግሞ ብሔራዊ የጥበቃ አባላትን ያንቀሳቀሱ ሲሆን ቴክሳስ ከዛሬ ጀምሮ በዓለ ሲመቱ እስኪያልፍ የግዛቲቱን የመንግስት መቀመጫ እንዲዘጋ ወስናለች፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ፣ በተለይ የምርጫ ውጤት ውዝግብ የነበረባቸው ግዛቶች ከፍተኛ ችግር ሊፈጠርባቸው እንደሚችል ተንታኞች ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በአሁኑ አመጽ ከሚፈጠረው ችግር ይልቅ አሳሳቢው ጉዳይ አመጹ ጥሎት የሚያልፈው አሻራ እና በቀጣይነት ሊኖር የሚችለው የጽንፈኝነት ጉዳይ መሆኑን ሲኤንኤን ያነጋገራቸው ተንታኞች ገልጸዋል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካፒቶል ላይ አመጽ በመቀስቀስ እንዲከሰሱ እና ከስልጣን እንዲወርዱ ከቀናት በፊት በኮንግረሱ ኢምፒችመንት የተወሰነባቸው ሲሆን ለሁለት ጊዜያት ኢምፒች በመደረግ በታሪክ የመጀመሪያው የዐሜሪካ መሪ ናቸው፡፡