በካፒቶል ሂል በተፈጸመው አመጽ በተባባሪነት የተጠረጠሩ በርካታ ፖሊሶች ታገዱ
የትራምፕ ደጋፊ ሰልፈኞችን ወደ ኮንግረሱ መሰብሰቢያ ስፍራ የመሩ ፖሊሶች መኖራቸው ተገልጿል
እስከ 15 በሚደርሱ ፖሊሶች ላይ ደግሞ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን ከስራ እስከማባረር እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል
ባለፈው ረቡዕ የትራምፕ ደጋፊዎች በዋሺንግተን ካፒቶል ሂል በፈጸሙት የአመጽ ድርጊት ተሳታፊ እና ተባባሪ እንደሆኑ የተጠረጠሩ በርካታ የፖሊስ አባላት ከስራ መታገዳቸውን የካፒቶል ሂል ፖሊስ ተጠባባቂ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
ተጠባባቂ ኃላፊዋ ዮጋናንዳ ፒትማን እንዳሉት የቪዲዮ ፣ የፎቶ እና ሌሎች ማስረጃዎችን በመፈተሸ ነው እርምጃው የተወሰደው፡፡ በማጣራት ሂደቱ አንድ ፖሊስ የትራምፕ መፈክር ያለበትን ኮፊያ አድርጎ አመጸኛ የትራምፕ ደጋፊዎችን አቅጣጫ እያሳየ ወደ ኮንግረሱ መሰብሰቢያ ሲመራ የሚያሳይ ቪዲዮ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ከሰልፈኞቹ ጋር በመሆን የ ’ሰልፊ’ ፎቶ ሲነሳ የሚያሳይ ቪዲዮ ተገኝቷል ነው የተባለው፡፡
ኤንቢሲ ኒውስ እንደዘገበው እገዳ ከተጣለባቸው ፖሊሶች በተጨማሪ ሌሎች ከ 10 እስከ 15 ፖሊሶች ደግሞ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ የካፒቶል ፖሊስ ተጠባባቂ ኃላፊዋ ዮጋናንዳ ፒትማን ፣ በእርሳቸው የሚመራው የፖሊስ ዲፓርትመንት ቪዲዮዎችን እና ሌሎች ማስረጃዎችን በጥብቅ እየመረመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የምርመራውን ውጤት ተከትሎ በወንጀሉ በተሳተፉ አባላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ከስራ እስከማባረር ሊደርስ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከካፒቶል ፖሊሶች አንዱ የሆነው እና በኢራቅ ጦርነት የተሳተፈው የቀድሞ ወታደር ዩጂን ጉድማን ፣ ስሙ በጀግንነት ተነስቷል፡፡ ዩጂን ጉድማን አመጸኞቹ ካፒቶል ሂልን ሰብረው ገብተው ሲያባርሩት ወደ ምክር ቤቱ እንዳይገቡ በተሳሳተ አቅጣጫ ሲመራቸው እንደነበር ተገልጿል፡፡
የካፒቶል ፖሊስ ኃላፊ የነበሩት ስቲቨን ሳንድ ፣ ባለፈው ረቡዕ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ (ካፒቶል ሂል) በፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ከተፈጸመው አመጽ ጋር በተያያዘ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡
በዕለቱ በተፈጠረው የአመጽ ድርጊት አንድ የካፒቶል ፖሊስን ጨምሮ 5 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡