ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ኢምፒችመንት የተካሔደባቸው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው
ከሳምንት በፊት ታህሣሥ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሺንግተኑ ካፒቶል ሂል የትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙት የአመጽ ድርጊት ጋር በተያያዘ በርካታ ትችቶችን ከማስተናገዳቸውም ባለፈ ፣ የፈጸሙት ድርጊት ትክክል መሆኑን መናገራቸው ደግሞ ይበልጥ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በዚሁ ድርጊታቸው ሳቢያ በ25ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከስልጣን እንዲነሱ የተወካዮች ምክር ቤቱ ቢወስንም ፣ ይህን ውሳኔ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ አልተቀበሉትም፡፡
ይህን ተከትሎ ፣ ትራምፕ አመጽ በመቀስቀስ ወንጀል ተከሰው ፣ በኢምፒችመንት ከስልጣን እንዲነሱ ምክር ቤቱ ትናንት ምሽት ወስኗል፡፡ በፕሬዝዳንቱ ድርጊት የተቆጡ ሪፓብሊካኖችም ጭምር ኢምፒች እንዲደረጉ (ከሰልጣናቸው እንዲነሱ) ድምጽ ሰጥተው ባጠቃላይ 232 ለ 197 በሆነ ድምጽ ኮንግረሱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ይህም ፕሬዝዳንት ትራምፕን በወንጀል ድርጊት ተከሰው ከስልጣን እንዲነሱ ለሁለተኛ ጊዜ ኢምፒችመንት የተካሔደባቸው በታሪክ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያደርጋቸዋል፡፡
ኢምፒችመንቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎቻቸው እንዲረጋጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አመጽ እና ረብሻ በሀገራችን ቦታ የላቸውም ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእኔ እውነተኛ ደጋፊ ፖለቲካዊ አመጽ አይቀሰቅስም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ ስልኢምፒችመንቱ ሕገ መንግስቱን እና ህሊናቸውን የተከተሉ አባላት የሰጡት ድምጽ ነበር ካሉ በኋላ ሀገሪቱ በሀገሪቱ ገዳዩ የኮሮና ቫይረስ እና የኢኮኖሚ ችግሮችም መኖራቸውን አንስተው ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ሴኔቱም በኢምፒችመንቱ እንዲሁም በሌሎች ችግሮችም ላይ ላይ ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በኮንግረሱ የኢምፒችመንት ውሳኔ ላይ ሴኔቱ የጆ ባይደን በዓለ ሲመት ከመፈጸሙ በፊት ድምጽ እንደማይሰጥ ተገልጿል፡፡ የሴኔቱ አብላጫ ወንበር ባለቤት የሪፓብሊካኑ መሪ ሚች ኮኔል በሰጡት መግለጫ ፣ ቀጣዩን ሳምንት ሁሉም አካላት ስርዓቱን በጠበቀ የስልጣን ሽግግር እና ሰላማዊ የሹመት ሥነ-ስርዓት ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው ሴኔቱ በኢምፒችመንቱ ላይ ድምጽ የሚሰጠው ከስልጣን ሽግግሩ በኋላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለ5 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የካፒቶል አመጽ በመቀስቀስ የተወቀሱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወንጀል መስራታቸው ተረጋግጦ በኢምፒችመንት ከስልጣን እንዲነሱ በሴኔቱ ከጸደቀ ፣ ከዚህ በኋላ በምርጫ መወዳደር አይችሉም፡፡