የትራምፕ ደጋፊዎች በመላው አሜሪካ ታጥቀው ለአመጽ ሊወጡ እንደሚችሉ ኤፍቢአይ አስጠነቀቀ
የተመራጩ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት በትራምፕ ደጋፊዎች አመጽ እዳይረበሽ ካፒቶል ሂል ዙሪያው እየታጠረ ነው
በትጥቅ ይታገዛል የተባለው አመጽ እስከ ባይደን በዓለ ሲመት ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ተገልጿል
የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት እስከሚፈጸም ድረስ በ50ው የአሜሪካ ግዛቶች በሚገኙ የመንግስት መቀመጫዎች እንዲሁም በዋሺንግተኑ የፌዴራል መንግስት መቀመጫ በትጥቅ የታገዙ አመጾች ሊኖሩ እንደሚችሉ ኤፍቢአይ አስጠንቅቋል፡፡
ይህም የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ካለመቀበል ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የደም መፋሰስ ሊያስከትል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ የምርጫው ውጤት ባልተዋጠላቸው ዶናልድ ትራምፕ ቀስቃሽነት ፣ ባለፈው ሳምንት በዋሺንግተን ካፒቶል ሂል ደጋፊዎቻቸው በፈጠሩት አመጽ አንድ ፖሊስን ጨምሮ 5 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እንዳስታወቀው የትራምፕ ደጋፊዎች የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ታይቀው ከዚህ ሳምንት ጀምሮ አመጽ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ፡፡ አመጹ የባይደን በዓለ ሲመት እስኪፈጸም ድረስ እንደሚቀጥልም ነው ቢሮው የገለጸው፡፡ በአመጹ ከሚሳተፉት መካከል ጽንፈኛ ቡድኖች እንደሚኖሩም የኤፍቢአይ ባለሙያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
የኤፒ ዘገባ እንደሚያመለክተው ፣ በ50ው የአሜሪካ ግዛቶች በመሳሪያ ትጥቅ ታግዞ የሚካሄደው አመጽ ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቢያንስ በዓለ ሲመቱ እስከሚፈጸምበት ጥር 12 ሊቀጥል ይችላል፡፡ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ (ካፒቶል ሂል) ደግሞ ከጥር 9 ጀምሮ እስከ ጥር 12 ሊቀጥል እንደሚችል ኤፍቢአይ አስታውቋል፡፡
ይህ ስጋት ይፋ የሆነው በበዓለ ሲመቱ ዝግጅት በሚል ፣ የባለፈውን ሳምንት አይነት አመጽ እንዳይፈጠር ፣ የካፒቶል ሂል ዙሪያ እየታጠረ ባለበት ወቅት ነው፡፡ አጥሩ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
ኤፍቢአይ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ በሚችሉ ሰልፎች እና አመጾች ላይ በማተኮር ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ በሰላማዊ መንገድ የሚካሄዱ ሰልፎችን ግን እንደማይከታተል ነው የገለጸው፡፡
በትናንትናው ዕለት ጆ ባይደን በሰጡት አስተያየት በካፒቶል ሂል ተገኝተው ቃለ መሀላ በመፈጸም አሜሪካን የመምራት ኃላፊነት ለመረከብ ስጋት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ በካፒቶል ሂል ሞት ያስከተለ አመጽ ከተካሄደ ከ 2 ሳምንታት በኋላ ጥር 12 ፣ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ምክትላቸው ሀሪስ በስፍራው ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትራምፕ የትዊተር ገጻቸው ከመዘጋቱ በፊት “ለጠየቃችሁኝ ሁሉ ፣ ጥር 20 በሚኖረው በዓለ ሲመት ላይ አልገኝም” ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህ ጽሁፋቸው አንድም የምርጫው ውጤት ትክክል አለመሆኑን ሁለትም እርሳቸው ስለማይገኙበት በዓለ ሲመቱ ላይ ደጋፊዎቻቸው አመጽ እንዲያስነሱ መልዕክት ለማስተላለፍ ሊሆን እንደሚችል ትዊተር ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ይህም አካውንታቸው (የትዊተር ገጻቸው) ለመዘጋቱ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡