ዲፕሎማሲ “መቆሚያው እዚህ ነው ብሎ መገመት አይቻልም…ድልድዩን ስንደርስ እንሻገረዋለን” አምባ. ዲና ሙፍቲ
የግድቡን ድርድር “ኮንጎም ይሁን ሌላ ሀገር ይምራው ለእኛ ምንም ችግር የለም ፤ የያዝነው አቋም ትክክል እስከሆነ ድረስ” ብለዋል
ሱዳኖች የኢትዮጵያን ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው “ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል
በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ውጥረት ከ 25 ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ፣ የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ክልል ዘመቻ ላይ በነበረበት ወቅት ሱዳን “ይገባኛል” የምትለውን ግዛት በኃይል ወረራ መያዟ ነው፡፡
በሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደረ ዲና ሙፍቲ ፣ ሱዳን የፈጸመችውን ድርጊት “ክህደት ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “ኢትዮጵያ ባላሰበችው እና ባልጠበቀችው መንገድ ፊቷን ወደ ሰሜን የሕግ ማስከበር ተግባር ስታዞር ከኋላ ተመታለች” ያሉት አምባሳደር ዲና ፣ ይህ ድርጊት ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሱዳንንም ህዝብ የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የማይመጥን ከመሆኑም ባለፈ የሀገራቱን ጥቅምም የሚጻረር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የድንበር ውዝግቡን በተመለከተ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች
ሱዳን ከኢትዮጵያ “በኃይል አስመልሻለሁ” የምትለውን ይዞታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለያዩ ሀገራት ልዑካንን በመላክ ማብራሪያ መስጠቷን ቀጥላለች፡፡ በተለይም ወደ አጎራባች የአፍሪካ ሀገራት እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት መሪዎቿን እና ሌሎች ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናትን በመላክ ጉዳዩን ለማሳወቅ በተደጋጋሚ በር አንኳኩታለች፡፡
ሱዳን በዲፕሎማሲው መስክ ሩጫዋን ባፈጠነችበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ምን እየሰራች እንደሆነ ከአል ዐይን ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፣ ኢትዮጵያ በዋናነት መልዕክት የምታደርሰው ለሱዳን ህዝብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “የሱዳን ህዝብ ኢትዮጵያ በችግሩ ጊዜ የምትደርስለት እና ሁል ጊዜ ከጎኑ የምትቆም መሆኑን ያውቃል” ያሉት አምባሳደር ዲና ፣ ለዚህም ከዓመት በፊት የሱዳንን የተለያዩ ኃይሎች ወደ አንድነት በማምጣት ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጫወቱትን ሚና እና በወቅቱ የሱዳን ህዝብ ያሳየውን ስሜት የቅርብ ጊዜ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡ “ያንን ስሜት ከምንም አለመቁጠር እና መካድ ማለት በዋናነት በሱዳን ህዝብ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ትልቁ መልዕክታችን ለሱዳን ህዝብ እንዲደርስ እንፈልጋለን” ሲሉም አክለዋል፡፡
አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልጋት ሰላም ፣ አንድነት እና ልማት መሆኑን በመጥቀስ ለጎረቤት እና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራትም ኢትዮጵያ ስለጉዳዩ እያሳወቀች መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ላሉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰቦች በኤምባሲዎች አማካኝነት ግምባር ቀደም ጉዳይ በማድረግ ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ፣ የማስረዳት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት፡፡
በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ውጥረት ዕልባት እንዲያገኝ ሱዳን በቅርቡ ከያዘችው ግዛት መውጣት እንዳለባት ኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመቷንም አምባሳደር ዲና አስታውሰዋል፡፡
ሱዳኖች “ይሄንን ያለአግባበብ የያዙትን ቦታ ለቀው ወደ ቦታቸው ይመለሱ ፤ የነበረውን የድንበር ልዩነት ከዚህ ቀደምም እየተነጋገርንበት ነው ያለነው ፤ አሁንም ተነጋግረን እንፍታው” የሚል መልዕክት እየተላለፈ እንደሚገኝ አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል፡፡ ጥሪ የቀረበላቸው ነባራዊው ሁኔታ እንዲመለስ ስለሆነ ፣ ሱዳኖች ይህን ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው “ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡ “ከእለታት አንድ ቀን አንተ ቤትህን ዘግተህ መንገድ ስትሔድ ለጉዳይ ፣ ቤትህን ከፍቶ ገብቶ ቤቴ ነው የሚልህ ሰው ምን አይነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ትችላለህ” በማለት የሱዳንን ድርጊት አውግዘዋል፡፡ ይህ የሀገሪቱ ተግባር እንኳን የሱዳንን ህዝብ ፣ የሱዳንን መንግስትም ጥቅም የማይወክል እና የሌላ ወገን ተልዕኮ መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ይሄን ለማረም አሁንም ጊዜው አልመሸም” ያሉም ሲሆን “ጎረቤት ሀገር ላይ ያለአግባብ የሚዘምት እና እምነት የሚያጎድል ኃይል ተገቢ ስራ እንዳልሰራ ሌሎች ሀገራት ከዚህ መማር አለባቸው” ብለዋል፡፡
ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚሰጠው ያነሱት አማባሳደር ዲና ዲፕሎማሲ ግን “የሚቀጥለው እስካስፈለገ ድረስ ነው ፤ መቆሚያው እዚህ ነው ብሎ መገመት አይቻልም” ካሉ በኋላ “ድልድዩን ስንደርስ እንሻገረዋለን” በማለት ተናግረዋል፡፡
ሕዳሴው ግድብ እና የዲአር ኮንጎ አደራዳሪነት
ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ዲና “ለአፍሪካ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን መፈለግ” ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ አቋም አረጋግጠዋል፡፡
የሕዳሴው ግድቡ ጉዳይ “በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል እንፈልጋለን” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ፣ እስካሁን በደቡብ አፍሪካ መሪነት የተሰራው ስራ ገንቢ እንደነበር ጠቅሰው ለዙህም ደቡብ አፍሪካን አመስግነዋል፡፡
ቀጥለውም “ቀጣይ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የምትሆነው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተመሳሳይ ሚና ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ታስገኛለች ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
ኮንጎ በግድቡ ጉዳይ ከግብፅ ጎን እንደምትቆም ከ 2 ወራት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ለግብፁ አቻቸው በላኩት መልዕክት ማረጋገጣቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አምባሳደር ዲናም ግብፅ እና ሱዳን የግድቡ ድርድር በኮንጎ መሪነት እንዲካሔድ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያና ኮንጎ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው እና ኮንጎ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በአካል ዘምተውም ጭምር ከህዝቡ ጎን መቆማቸው በሀገሪቱ ህዝብ የሚዘነጋ እንዳልሆነ አምባሳደር ዲና አንስተዋል፡፡
አክለውም “የእኛ ጉዳይ የዓባይን ውሃ በፍትሓዊነት መጠቀም ነው ፤ ኢትዮጵያ 86 በመቶ ከራሷ ከሚፈልቀውን ውሃ ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚከለክል አቋም ሊኖር አይችልም” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያሳፍራት አቋም የላትም ያሉት አምባሳደር ዲና “በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ኮንጎም ይሁን ሌላ ሀገር ይምራው ለእኛ ምንም ችግር የለም ፤ የያዝነው አቋም ትክክል እስከሆነ ድረስ” ሲሉ በኮንጎ አደራዳሪነት የሚያሳስብ ጉዳይ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ “አፍሪካዊ መፍትሔን ማዕከል አድርገን የኮንጎን አመራር ይዘን ድርድሩን እንቀጥላለን” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ 34ኛውን የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን እና በጉባዔው ላይ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና መረጋጋት ችግሮችን ጨምሮ የሌሎችም ቀጣናዎች ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡