“በድንበር ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶች የአዲስ አበባና የካርቱም አቋም አይደሉም” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የሁለቱ ሀገራት የድንበር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት የጋራ ውይይት ያደርጋል ተብሏል
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ በሚፈጠሩ ግጭቶች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ገለጸ
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ወታደሮች እና “በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች” መካከል በተፈጠረው ግጭት ላይ ያተኮረ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በመግለጫቸውም ማክሰኞ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሱዳን ወታደሮች በ ‘ጃባል አቡጢዩር’ አካባቢ ቅኝት አድርገው ሲመለሱ “ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው አድፍጠው በነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል፡፡ በዚህም ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋት እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ላይ መሰል ግጭቶች ከዚህ ቀደምም እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ይህ ክስተት የአዲስ አበባና የካርቱም አቋም አይደለም ብለዋል፡፡ ሰፊ ድንበር በሚጋሩት በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ለረዥም ዘመናት የቆየ ወዳጅነት መኖሩን እና ሀገራቱም በበርካታ የጋራ እሴቶች የተሳሰሩ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሱዳን ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች የተፈጠረውን ግጭት ጨምሮ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ጉዳይ ላይ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ላለፉት ጊዜያትም ውይይት ሲደረግ መቆየቱንና በዚህም ዘላቂ እልባት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና ያብራሩት፡፡
በድንበር አካባቢ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የሚሊሻዎችና የታጣቂዎች እንጂ የሁለቱን ሀገራት የቆየ አብሮነትና ወዳጅነት እንዲሁም የሀገራቱን አቋም የሚገልጹ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በበጎም በመጥፎም ጊዜ አብሮነታቸው የጠነከረ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሱዳን ሪፐብሊክ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ የተመራው የልኡካን ቡድን እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ፣ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ድንበር የማካለል ጉዳይ ታሪካዊ ዳራውን በጠበቀ፣ ወቅታዊ ሁኔታውን ባገናዘበ፣ "ያገባኛል" የሚሉ አካላትን ሙሉ ተሳትፎ ባካተተ መልኩ እንደሚከናወን በውይይቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ይሁን እንጂ በድንበር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት ውይይት እንደሚያደርግ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡