''ሱዳን አሁንም ወደቦታዋ ትመለስ ነው የእኛ አቋም'' አምባሳደር ዲና
ዲፕሎማሲያዊው ጥረት አስፈላጊ እስከሆነበት ድረስ እንደሚቀጥል አምባሳደር ዲና ተናግረዋል
ሱዳን ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ እንደማትቀበል የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ገልጸዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ በዋናነት የኢትዮ-ሱዳንን እና የሕዳሴ ግድቡ ላይ ትኩረት አድርገው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያና የሱዳንን የድንበር ውጥረት በተመለከተ ''ፊታችንን ወደ ሰሜን ስናዞር ሱደሰኖች ወደኛ መጡ'' ያሉት አምባሳደር ዲና ከዚህ በፊት የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት የተቋቋመ የፖለቲካ ኮሚቴ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አንስተዋል፡፡
አሁንም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የማደራደር ጥያቄ ያነሱ አካላት መኖራቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ ''እናደራድር ያሉ አካላትን እናመሰግናለን ፣ ነገር ግን ሱዳን አሁንም ወደቦታዋ ትመለስ ነው የእኛ አቋም'' ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየተከተለች መሆኑ ምን ውጤት አስገኘ? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ''ይህ ሀገር ለሰላም የቆመ ነው ፤ ትልቅ ቁመና ያለው ሀገር ነው የሚል ድጋፍ ማግኘት ተችሏል፡፡ይህ በጣም ትልቅ አቅም ነው'' ሲሉ መልሰዋል፡፡ ዲፕሎማሲያዊው ጥረት እስከመቼ እንደሚቀጥል የተጠየቁት አምባሳደር ዲና “እስከሚያስፈልግ ድረስ ይቀጥላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ያሲን ኢብራሂም ትናንት ከአል አረቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ ሱዳን ከቀድሞው ይዞታዋ አልፋ ከገባችበት ጦሯን እንድታስወጣ እና ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ያቀረበችውን ጥያቄ ሱዳን እንደማትቀበል ገልጸዋል፡፡ “ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አንቀበልም” ያሉት ሚኒስትሩ ፣ይባስ ብለው ፣ “ኢትዮጵያ መልቀቅ ያለባት ገና ያላስመለሱት ይዞታ” መኖሩን አንስተዋል፡፡
በቀጣይነት ጦርነት ስለመቀጠል ያላቸውን ሀሳብ በተመለከተ ሲጠየቁ “ከያዝነው ቦታ አንወጣም ፤ ይዞታችንን እንደያዝን በድርድር መፍታት እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ “ይህ ካልሆነ ነው ወደ ቀጣይ እርምጃ ልንሄድ የምንችለው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በዛሬው መግለጫቸው ''ነገሩን በሰላም ብቻ ነው መፍታት የምንፈልገው ፤ ለድርድሩም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠናል ፤ ኢትዮጵያ አዲስ አቋም አይደለም ያንጸባረቀችው'' ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የድንበሩም ይሁን የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር ብቻ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ለብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ማብራራታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ግድቡ ፣ ሁለቱንም ሀገራት እንደማይጎዳ ለዶሚኒክ ራብ ያብራሩት አቶ ደመቀ የአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪ ወገን የጀመረው መንገድ እንዲሳካ ኢትዮጵያ ፍላጎቷ መሆኑንም እንደነገሯቸው አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡