“አሜሪካ ወደ ዓለም መድረክ ተመልሳለች” ፕሬዝደንት ጆ ባይደን
ፕሬዝዳንት ባይደን በብዙ ጉዳዮች ከትራምፕ የተለየ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚከተሉ አስታውቀዋል
ለሳዑዲ አረቢያ መራሹ የየመን ወታደራዊ ዘመቻ አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ ማቆሟን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ በዋና ዋና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ፣ አሜሪካ ወደ ዓለም መድረክ ተመልሳለች ብለዋል፡፡ ይህም ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲ ትልቅ ለውጥ ያሳየ እንደሆነ ነው የሚገለጸው፡፡
ባይደን በንግግራቸው የምያንማር ወታደራዊ መሪዎች መፈንቅለ መንግስቱን እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ለሚመራው የየመን ወታደራዊ ዘመቻ የአሜሪካ ድጋፍ ማብቃቱንም አሳውቀዋል፡፡
በየመን እየተካሔደ ያለው ጦርነት ማብቃት አለበት ያሉት ባይደን ላለፉት 5 ዓመታት በሳዑዲ መሪነት የሚደረገውን ዘመቻ ከዚህ በኋላ አሜሪካ እንደማትደግፍ ገልጸዋል፡፡ ጦርነቱ በአረብ ባህረ ሰላጤዋ ሀገር የመን ሰብዓዊ እና ስትራቴጂካዊ ችግሮች ከልክ በላይ እንዲባባሱ ማድረጉን በመግለጽ ፣ ዲፕሎማሲ ፣ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በየመን ጉዳይ የተወሰደው እርምጃ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አሜሪካ ከምታደርጋቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች አንዱ እንደሆነም ነው ባይደን የገለጹት፡፡
ባይደን እንዳሉት ምንም እንኳን አሜሪካ በሀገሪቱ የሚደረገውን ዘመቻ መደገፏን ብታቆምም ፣ ሀገሪቱን መቀመጫቸው አድርገው ጥቃት የሚፈጽሙ እንደ አልቃኢዳ ያሉ አሸባሪዎችን ግን መዋጋቷን ትቀጥላለች፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት በየመን በነበረው ጦርነት ከ110,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይታመናል፡፡
በሀገሪቱ ጦርነት የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2014 በሀገሪቱ ያልተጠናከረ መንግስት እና በሀውቲ አማጺያን መካከል ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ሳዑዲ መራሹ ጥምር ሀይል በሀውቲ አማጺያን ላይ የአየር ጥቃት መፈጸም ጀምረው ችግሩ ይበልጥ እንደተባባሰ እስከዛሬ ቀጥሏል፡፡
አሜሪካ የምትቀባላቸውን ስደተኞች ቁጥር መጨመር እና ከጀርመን የአሜሪካን ጦር የማስወጣት ዕቅድን መቀልበስ ጨምሮ ከትራምፕ አስተዳደር የተለዩ ሌሎች የውጭ ፖሊሲዎችንም ባይደን ይፋ አድርገዋል፡፡