አሜሪካን ከመከፋፈል ማውጣት እና ኮሮናን መከላከል ቀዳሚ ትኩረታቸው እንደሚሆን ባይደን ገለጹ
“አሁን ጊዜው አሜሪካን የማዳን ነው” ሲሉ 46ኛው የአሜሪከ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ጆ ባይደን ተናግረዋል
እስከ አሁን ሽንፈታቸውን ያልተቀበሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ነገ ክስ እጀምራለሁ ብለዋል
አሜሪካን ከመከፋፈል ማውጣት እና ኮሮናን መከላከል ቀዳሚ ትኩረታቸው እንደሚሆን ባይደን ገለጹ
በዘረኝነት የሚተቹት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መሪነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ልዕለ ሀያሏ ሀገር አሜሪካ በከፍተኛ መከፋፈል ውስጥ እንደቆየች የተካሔደው ምርጫ 2020 ፕሬዝዳንቱ ኋይት ሀውስን እንዲለቁ አስገድዷል፡፡
ከ40 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን ያገለገሉት ጆ ባይደን አሁን ደግሞ ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲያገለግሉ ታሪካዊውን ምርጫ በማሸነፍ የፖለቲካ ልምድ ከሌላቸው ትራምፕ የኋይት ሀውስን ቁልፍ ለመቀበል ተዘጋጅተዋል፡፡
በዘመነ ትራምፕ በአሜሪካ ከነገሰው የዘረኝነት መከፋፈል በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም በዓለም የአሜሪካን ያህል የተጠቃ ሀገር የለም፡፡ ለዚህም ነው ባይደን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር “አሁን ጊዜው አሜሪካን የማዳን ነው” ያሉት፡፡
ባይደን ፕሬዝዳንትነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ በዴላዋር በተዘጋጀ ስነስርዓት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ኮሮና ቫይረስን መቆጣጠር ፣ ዘረኝነትን መዋጋት ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ከዋና ዋና ተግባሮቻቸው መካከል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ምክትላቸውም በነዚህ ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ትራምፕ የጣሉትን የፓሪስ ስምምነትዳግም ያነሱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለአረንጓዴ ኃይል ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለጹት ባይደን ለታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ 1. 7 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚመድቡ አስታውቀዋል፡፡ በግል ኢንቨስትመንቶች የሚሰሩትን ጨምሮ በጀቱ እስከ 5 ትሪሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡
ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ስራችን የምንጀምረው ኮቪድ-19ን በመቆጣጠር ነው ብለዋል፡፡ “ይህን ቫይረስ መቆጣጠር እስካልቻልን ኢኮኖሚያችንን እንዲያንሰራራ ማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮቻችንን ማከናወን አንችልም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ቫይረሱ ከ235,000 በላይ አሜሪካውያንን ህይወት ነጥቋል፡፡ 20 ሚሊዮን ህዝብ ስራውን እንዲያጣም ያደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ ዓመታት ሀገሪቱን 16 ትሪሊዮን ዶላር ሊያሳጣት እንደሚችልም ተገምቷል፡፡ ባይደን ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚያቋቁሙትን ቡድን ነገ እንደሚያሳውቁም ይጠበቃል፡፡
ይህ ዓመት ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ ከፍተኛ ተቃውሞ ከተስተናገደባቸው እና መከፋፈል ከነገሰባቸው ዓመታት አንዱ ነው፡፡ በተለይ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ ዘረኝነትን በመቃወም ከአሜሪካ አልፎ በመላው ዓለምም በርካታ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡
የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድንም ዘረኝነትን ማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ሲቀሰቅሱ ነበር የከረሙት፡፡ ጆ ባይደን እና የመጀመሪያዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ለመሆን ያሸነፈችው ካማላ ሀሪስም በንግግራቸው ዘረኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ የገለጹ ሲሆን የኮሚዩኒቲ ፖሊስን ስራ እንደሚያጠናክሩ ባይደን ተናግረዋል፡፡
የሚቃወሙንን እንደጠላት መመልከት ሊቆም ይገባል ያሉት ባይደን ሁሉንም አሜሪካውያን በእኩልነት እንደሚያገለግሉ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመጠበቅ እንደሚሰሩም ነው የገለጹት፡፡ ሀገሪቱን ከመከፋፈል በማውጣት አንድነጸዋን መጠበቅ ዋነኛው ትኩረታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ከ74 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የመረጣቸው ጆ ባይደን ከፍተኛ ቁጥር ባለው ህዝብ በመመረጥ ክብረወሰን ይዘዋል፡፡ ከሁት ወራት በኋላ 78ዓ ዓመታቸውን የሚያከብሩት ባይደን በሀገሪቱ ታሪክ በእድሜ ትልቁ ፕሬዝዳንትም ይሆናሉ፡፡
ከ538 ወካይ ድምጾች 279 ድምጾችን ማግኘታቸው የተረጋገጠ ሲሆን አንዳንድ ሚዲያዎች ደግሞ ገና ያልተረጋገጠውን አሪዞናንም እንዳሸነፉ በመቁጠር 290 ወካይ ድምጾችን እንዳገኙ ዘግበዋል፡፡ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ለባይደን እና ሀሪስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉት ትራምፕ አሁንም ድረስ ሽንፈታቸውን ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ በሀሰት ባይደን ማሸነፋቸው ተገልጿል ያሉት ትራምፕ ውድድሩ ገና አልተጠናቀቀም ብለዋል፡፡
ቆጠራው በትክክል መከናወኑን የአሜሪካ ህዝብ እስኪያውቅ ድረስ አላርፍም ሲሉም ትራምፕ ገልጸዋል፡፡ ከነገ ሰኞ እለት ጀምሮ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ የህግ ክፍል ህጋዊ ሂደቶችን እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡
የባይደን ማሸነፍ ይፋ በተደረገበት ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቨርጂንያ የጎልፍ ጨዋታ ላይ ነበሩ
የባይደን ማሸነፍ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ባልተለመደ መልኩ በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ባይደን መካከል ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልተፈጠረ የሲኢንኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር ፕሬዝዳንቱ ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ እያግባባቸው ስለመሆኑም ታማኝ ምንጮችን በመጥቀስ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡