የአሜሪካና የዩኬ ኢምባሲዎች በትግራይ ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቀረቡ
በትናንትው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ በሚገኘው መከላከያ ላይ ጥቃት ደርሷል ብለዋል
ኢምባሲዎቹ በፌደራልና በትግራይ ክልል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል
ኢምባሲዎቹ በፌደራልና በትግራይ ክልል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል
በአዲስ አበባ የሚገኙት የአሜሪካና የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) ኢምባሲዎች በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲረግብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢምባሲዎቹ ጥሪውን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል በሚገኘው መከላከያ ሃይል ላይ ህወሓት ጥቃት መሰንዘሩንና መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ ትናንት ሌሊት ማስታወቁን ተከትሎ ነው፡፡
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
የትግራይ ክልል በበኩሉ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚደረግ በረራ ማገዱንና የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ኢምባሲ በፌስቡክ ገጹ “ውጥረቱ አስቸኳይ መርገብ አለበት፤ በሁለቱም ወገን የተመጠነ ምላሽ ለኖር ይገባል፡፡ሁለቱም አካላት የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት እንዲያስቀድሙ እናበረታታለን” ብለዋል፡፡
የዩኬ ኢምባሲ በበኩሉ በትግራይ ያለው ውጥረት እንዲረግብ የአለምአቀፍ ማህበረሰቡን ጥሪ መቀላቀሉን ገልጿል፡፡ ኢምባሲው ሁለቱም አካላት የሰላማዊ ሰዎችን እንዳይጎዱ ማድረግ አለባቸው ብሏል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፤ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡ ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡