“የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ
ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ገለጹ
“የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሕወሐት ሰነዘረ ያሉትን ጥቃት በማስመልከት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰጡትን መግለጫ “ውድ የሀገሬ ህዝብ ሆይ ዛሬ ከሃዲ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ወግተዋል” ሲሉ ነው የጀመሩት።
ላለፉት 20 ዓመታት የቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆን ሀገሬን ወገኔን ህዝቤን ብሎ በብዙ ሺዎች መስዋዕትነት ከፍሎ ቆስሎ ደምቶ ሀገሩንና ህዝቡን የታደገው የመከላከያ ሰረዊት ላይ ዛሬ ምሽት ከመቀሌ ጀምሮ በበርካታ ስፍራዎች በካሃዲው ኃይሎች እና ባደረጁት ኃይል ጥቃት ተፈፅሞበታል ብለዋል።
ይህጥቃት በሀገራችን እስካሁን ከደረሱት ጥቃቶች እጅግ አስነዋሪ የሚያደርገው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰላም ለማስከበር በተለያዩ ሀገራት በተሰማራበት በውጭ ኃይል እንኳን አጋጥሞት በማያውቀው ሁኔታ በገዛ ወገኑ ከጀርባው ጥቃት መፈጸሙ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይህም ጥቃት ብዙዎች እንዲሰዉ እና እንዲቆስሉ አድርጓል ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ ሕወሐት እስካሁን በንጹኃን ላይ ጥቃት ሲፈጽም እንደቆየ እና ይህም የመከላከያ ሰራዊት እንዳይረጋጋ እና ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲበተን ታልሞ የተደረገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ኢትዮያን ከውጭ ኃይል ጋር ተባብሬ እወጋለሁ ሲል የነበረው የሕወሐት ኃይል በከፍተኛ ትዕግስት በቆየው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም የተናገረውን በተግባር ጀምሯል ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ የፈፀሙት ጥቃት በአማራ ክልል በነበረው ኃይል ተመክቷልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ቀድመው ባሰለጠኑት ባሰማሩት ኃይል በመላ ሀገራችን በተለያየ ስፍራ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ ስለሚችል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሊሻው ከፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም በየአካባቢያችሁ ከሚገኝ የመከለከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር ቀያችሁን ሰፈራችሁን እንድትጠብቁ አሳስባለሁ” ሲሉም ለህብረተሰቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል። ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ “የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል” ብለዋል፡፡
ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗልም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
“የትግራይ ህዝብ ..ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ሀገርህን ከነዚህ ከሃዲ ኃይሎች እንድትከላከልና በንቃት እንድትጠብቅ አሳስባለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
“የመከላከያ ሰራዊት ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መለዮውን ሀገሩንና ህዝቡን እንዲከላከል ለሚከፍለው መስዋዕትነት ዛሬም እንደተለመደው በታሪኩ ውስጥ የሚታሰብ መሆኑን እገልፃለሁ” ብለዋል።
ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሳዘኝ አሳፈሪም ተግባር ቢሆንም “ዛሬም እንደተለመደው በተደመረ በተባበረ ክንድ ይህንን ከሃዲ ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈርና ለመደምሰስ እስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልፃለሁ” በማለትም ተናግረዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አስፈላጊው መረጃ በየጊዜው በሚመለከታቸው የመንግስት አከላት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ር/መስተዳድር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ የፌዴራል መንግስት ጦርነት ሊከፍትብን ሁሉም የመከላከያ ዕዞች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል ያሉ ሲሆን የትግራይ ኃይልም ለጦርነት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡