ከምሽቱ 4 እስከ 5 ሰዓት በአማራ ክልል ላይ ከሕወሐት ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ክልል አስታወቀ
የትግራይ ክልል ባወጣው መግለጫ የትግራይ አየር ክልል መዘጋቱን እና የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ መከልከሉ ገልጿል
በአማራ ክልል በሶሮቃ እና በቃራቀር አካባቢ የተሰነዘረው ጥቃት በልዩ ኃይል ተመክቷል ር/መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ
ከምሽቱ 4 እስከ 5 ሰዓት በአማራ ክልል ላይ ከሕወሐት ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ክልል አስታወቀ
ከምሽቱ ከ4 እስከ 5 ሰዓት አካባቢ በሰሜን እዝ ካምፖች ዲፖዎች እና የተለያዩ ይዞታዎች ላይ የትግራይ ሚሊሻ ጥቃት መሰንዘር ጀምሯል ሲሉ የአማራ ክልል ር/መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ለአማራ ቲቪ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ትጥቀቅ የመቀማት ሙከራም ተደርጓል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አማራ ክልልም ላይ በሶሮቃ እና በቃራቀር አካባቢ ጥቃት ሰንዝሯል ብለዋል፡፡ የተሰነዘረው ጥቃት በክልሉ ልዩ ኃይል እንደተመከተም ነው የገለጹት፡፡
ዓላማው ዲፋክቶ ስቴት (ሙሉ ዕውቅና ያላገኘ ሀገር) መመስረት ነው ያሉት አቶ ተመስገን ፤ ይህ ግን አይሳካም ብለዋል፡፡
በሕወሐት ሚሊሻ ከበባ ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዓባላትን ከከበባ ማውጣት እንደተቻለ በመግለጽ አንዳንድ መሳሪያዎችንም ወደኛ ማውጣት ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከከበባ የወጡት ተመልሰው ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ለውጊያ እንዲዘጋጁ አድርገናል ብለዋል፡፡
ይህንን ኃይል (ይሕወሐትን ኃይል) ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስርዓት ለማስያዝ የአማራ ክልል ከፌዴራል ኃይል ጋር የሚሰራ ይሆናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህም ሁሉም የአማራ ሕዝብ ፣ ልዩ ኃይል ፣ ፖሊስ ፣ ሚሊሻ እና ሁሉም የጸጥታ ኃይል በያለበት አካባቢውን እየጠበቀ ጥቃቱን ለመመከት እንዲዘጋጅ መታዘዙን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የሚመራ ኮማንድ ፖስት መኖሩንም ነው የተናገሩት፡፡
በተለያየ ምክንያት ከሰራዊቱ ለተቀነሱ የቀድሞ አባላትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በቀጣይ በሚኖሩ ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግስት መግለጫ ይሰጣል ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት በበበኩሉ ባወጣው መግለጫ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኘውን ኃይል በመላክ የፌዴራል መንግስት ሊያስወርረን እየተዘጋጀ ነው ብሏል፡፡
የትግራይን የአየር ኃይል ክልል ጥሶ መግባት የተከለከለ ነው ያለው መግለጫው ማንኛውም የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ የተከለከለ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡ ይህ ከተጣሰ እርምጃ እንደሚወሰድ በክልሉ ሚዲያዎች አማካኝነት የቀረበው መግለጫ ያመለክታል፡፡ በትግራይ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደማይኖርም ነው በመግለጫው የተጠቆመው፡፡
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ትናንት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የፌዴራል መንግስት ጦርነት ሊከፍትብን ሁሉም የመከላከያ ዕዞች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል ያሉ ሲሆን የትግራይ ኃይልም ለጦርነት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡