መንግስት “ሉአላዊነት የሚገዳደር” ሁኔታ በመኖሩ አስቸኳይ አዋጅ ማወጁን ገልጿል
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስት በትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው በሁለቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡
በትግራይ ክልል ህገመንግስትንና የህዝብ ሰላምና አደጋ ላይ የሚጥል፣የሀገርን ሉአላዊነት የሚገዳደር፤ የፌደራል መንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት የሚያደናቅፍ ሁኔታ በመከሰቱ ምክንያት መታወጁ ተገልጿል፡፡
“…የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ…” እንዲቻል እንደታወጀ መግለጫው አብራርቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል በሚገኘው መከላከያ ሃይል ላይ ህወሓት ጥቃት መሰንዘሩንና መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ ትናንት ሌሊት አስታውቀው ነበር፡፡
መግለጫው ለስድስት ወር የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚስፈጽም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግበረኃይል“ መቋቋሙን ገልጿል፡፡
የትግራይ ክልል በበኩሉ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚደረግ በረራን ማገዱንና የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡ ክልል በተከታታይ በሰጠው መግለጫ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የጠቀሰ ቢሆንም ነገርግን አስገዳጅ ሁኔታ ከመጣ ለጦርነት መዘጋጀቱንም አስታውቆ ነበር፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፤ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡ ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡