የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ አስተላለፉ
“ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግ ነው”- አቶ አገኘሁ
ማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሳሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ይክተት ብለዋል
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው “ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ ነው” ብለዋል።
“ሕዝቡ ከጎናችን እንዲሆን ባስተላለፍነው መልዕክት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ረገድ ከጎናችን ሆኗል” ያሉት አቶ አገኘሁ፤ ለዚህም ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
“ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ “ክልሎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ታሪካዊ ነው” ብለዋል።
የክልሉ ተመላሽ የሠራዊት አባላትና የጦር መኮንንኖች ሠራዊቱን ተቀላቅለው እየተፋለሙት እንደሚገኙም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
“ህወሓት በውጊያው ከሕፃናት እስከ አዛውንት ድረስ እያሰለፈ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን እያስጨረሰ ነው፣ ጦርነት የማያውቁ ሕፃናት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“የህወሓት ዓላማ የአማራን ሕዝብ ለማጥቃትና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያለመ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ “በራያና በጠለምት ግንባሮች የቡድኑ ጀሌዎች እንደ ቅጠል እየረገፍ ነው” ሲሉም ጠቅሰዋል።
“በሕዝቡ፣ በልዩ ኃይሉና በመከላከያ ሠራዊት ህወሓትን የመምታት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የተናሩሩ ሲሆን፤ “ይህ ኃይል እስካልጠፋ አናርፍም፤ ጦርነቱ የአማራን ሕዝብ ሕልውና የምንታደግበት ነው” ብለዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው በክልሉ ውስጥ የማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሣሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ማዕከል እንዲከት የክተት ጥሪ አስተላፈዋል።
“የክተት ጥሪው አማራንና ኢትዮጵያን የመታደግ ጥሪ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ “ሁሉም የክተት ጥሪውን ተቀብሎ ለፀረ ህወሓት ዘመቻ መዘጋጀት አለበት” ብለዋል።
“ሀገር የማፈረስ ዓላማ ያለውን ኃይል በተባበረ ክንድ መደምሰስ አለብን ” ያሉት አቶ አገኘሁ፤ “ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን ከሀዲ ቡድን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሁሉም መነሳት አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቁ በኋላ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመጀመሩ ግጭቱ መከሰቱ ይታወቃል።
ለ8 ወራት የቆየው ግጭት በፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈታ በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ መንግስት መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወቃል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል ለሚሉ አካላት ለማሳየትና ተጨማሪ ኪሳራ ሳይደርስ የትግራይ ቀውስ በውይይት እንዲፈታ በማቀዱ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
የመንግስት ጦር መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ሮይርስ ዘግቦ ነበር፤ የህወሓት ኃይሎች ለወራት በአማራ ክልል ስር የነበሩት ኮረምና አላማጣን መልሶ ለመቆጣጠር ሙከራዎችን አድርጓል።
ይህን ተከትሎም የአማራ ክልል መንግስት የህወሓት ኃይሎች ወረራ ፈጽመውብኛል በማለት ሌሎች ክልሎች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ግጭቱ ከአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች አልፎ ወደ አፋር ክልል ተስፋፍቷል፤ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የደቡብና የሲዳማ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የጸጥታ ሃይላቸውን ወደ ስፍራው አሰማርተዋል።
የፌደራል መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መንግስት ተኩስ አቆሞ እያለ የህወሃት ኃይሎች አሁንም በአማራ ክልል አካባቢ ተኩስ ከፍተዋል፤ መንግስት ተኩስ አቁም ያወጀው ለህዝቡ ሰላም ለመስጠት ሲል እንጅ የግጭት ቦታ ለመቀየር አልነበረም በማለት ምእራባውያን በህወሃት ላይ ያላቸውን አቋም ተችቷል።