የኦሮሚያ ክልል የ”ህግ ማስከበር ዘመቻ”ውን ለማገዝ የጸጥታ ሃይል ማሰማራቱን ገለጸ
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል መውጣቱ ይታወሳል
የአማራ ክልል መንግስት ተደቅኖብኛል ያለውን የህልውና አደጋ ለመከላከል የኦሮሚያ ክልልና ሌሎች ክልሎች ጥሪውን መቀበላቸውን አስታውቋል
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጸጥታ ኃይል የሀገር መከላከያ ሰራዊትን “የሕግ ማስከበር ዘመቻ”ን መቀላቀሉን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮ አስታወቀ፡፡
የቢሮ ኃላፊው አቶ ጌታቸው ባልቻ የክልሉ ጸጥታ ኃይል በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻን መቀላቀሉን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል፡፡
“ጁንታው እስኪጠፋ የሕግ ማስከበሩን ስራ ክልሉ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉል አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለአልአይን አማርኛ እንዳሉት የጸጥታ ኃይሉም፤ ሕዝቡም በዚህ ዘመቻ ይሳተፋል፡፡ “በሀገር ላይ የመጣን አደጋ በጋራ እንመክታለን“ ያሉት ኃላፊው የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች የህወሃት ሃይልን ለመዋጋት መሰማራታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ጌታቸው ባልቻ ክልሉ እና ሕዝቡ ይህንን የሚደርገው የሀገር መከላከል ሃላፊነት ስላለበት መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ይህንን ሀገርን የማዳን ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት አቶ ጌታቸውይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
አዲስ የተቋቋመው የሲዳማ ክልልም መከላከያ ሰራዊትን የሚያግዝ የጸጥታ ሃይል በዛሬው እለት መንቀሳቀሳቸውን ታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቁ በኋላ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመጀመሩ ግጭቱ መከሰቱ ይታወቃል፡፡
ለ8 ወራት የቆየው ግጭት በፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈታ በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ መንግስት መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወቃል፡፡
የመንግስት ጦር መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ሮይርስ ዘግቦ ነበር፡፡ በትናንትናው እለት የህወሓት ኃይሎች ለወራት በአማራ ክልል ስር የነበሩት ኮረምና አላማጣን መቆጣጠራቸውም ተዘግቦ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት ዛሬ በሰጠው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች “ በራያ አካባቢ አላማጣ፣ ኮረም እና ባላ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ፣ዛታ እና አበርገሌ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ ከፍቶብናል” ስለሆነም ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል ሲል አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ግዛቸው ሙሉነህ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች ተደቅኖብናል ያሉትን የህልውና አደጋ ለመከላከል ጥሪውን መቀበላቸውን አስታውቋል፡፡