በህወሓት የተከፈተበትን ወረራ ከመከላከል አልፎ በግልጽ ማጥቃት መጀመሩን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ
ህወሓት በራያ፣ በዋግ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ መክፈቱንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት
ከዚህ በላይ መታገሱ የከፋ ዋጋ ያስከፍላል ያሉት የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ “ከዛሬ ጀምሮ ከመከላከል አልፈን ግልጽ ማጥቃት ጀምረናል” ብለዋል
የፌዴራል መንግሥት ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ ይፋዊ ወረራ ከፍቶብኛል ያለውን ህወሓትን ከዛሬ ጀምሮ በግልጽ ማጥቃት መጀመሩን አማራ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡
“አሸባሪው ትህነግ ከስህተቱ ተምሮ ሕዝብን ከከፋ ስቃይ መታደግ ሲገባው በአማራ ክልል ግዛቶች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፍቶብኛል” ሲል የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው፡፡
“አሸባሪው ቡድን በራያ አካባቢ አላማጣ፣ ኮረም እና ባላ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ፣ ዛታ እና አበርገሌ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ ከፍቶብናል” ያሉት አቶ ግዛቸው በወረራው “ካህናትን፣ አዛውንቶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ከፊት በማሰለፍ ነውረኝነቱን አሳይቷል” ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት የአሸባሪውን ወረራ ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው “ከዚህ በላይ ትዕግስት የከፋ ዋጋ ስለሚያስከፍል ከዛሬ ጀምሮ ከመከላከል አልፈን ግልጽ ማጥቃት ጀምረናል”ም ነው ያሉት፡፡
አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው የክልሉ መንግሥት የአሸባሪውን አቅም በሚገባ እንደሚያውቀው ጠቁመው በአጭር ቀን ወደ መጣበት ይመለሳልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ እስካለ ድረስ ለአማራ ሕዝብ እና ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የህልውና ዘመቻው የተራዘመ ጊዜን ስለሚጠይቅ አስፈላጊው ዝግጅት ጎን ለጎን እንደሚቀጥልም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ኦሮሚያን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች የሕልውና ዘመቻውን ጥሪ በአዎንታ ተቀብለው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡
ህወሓት በዓለም አቀፍ ተቋማት እና ብዙኃን መገናኛዎች በኩል መጠነ ሰፊ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ ድጋፍ ማድረግ እና በአንድ መቆም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ማድረጋቸው በተገለጸበት መግለጫ ነጋዴውን ጨምሮ ሁሉም ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
“ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት ይቻል ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ሰዓት የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ለኦፕሬሽኑ ስኬት ሲባል መልስ የማይሰጥባቸው ስለሚሆኑ በትዕግስት መጠበቅ ተገቢ ነው” ሲሉም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በየደረጃው ባሉና በሚመለከታቸው የክልሉ የአስተዳደር አካት መግለጫ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት በራያ በኩል በከፈተው ጥቃት አላማጣን ለመቆጣጠር መቻሉን ሮይተርስን የመሳሰሉ የውጭ ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡