አምነስቲ በአማራ ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል ያለውን ጭፍጨፋ እንዲጣራ ጠየቀ
አምነስቲ በምዕራብ ወለጋ ህጻናት ጭምር መገደላቸውን ማረጋገጡን ገልጿል
አምነስቲ በአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰ መሆኑንም ጠቅሷል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ አዲስ የተወለዱ ህጻናት ጭምር መገደላቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።
ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቀበሌዎች የተፈጸመው ጭፍጨፋ በገለልተኛ አካል እንዲጣራም ጠይቋል፡፡
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ከ 400 በላይ የአማራ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባቸው ገልጿል፡፡ ይህንን ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲያስመሩ ምሩም አምነስቲ ጠይቋል።
ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በተፈጸመው ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሴ ሙቼና “በቶሌ የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ፣ ገዳዮቹ ለሰው ልጅ ሕይወት ምንም ደንታ እንደሌላቸው ያሳዩበት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሯ ይህ ግድያ የተፈጸመው መንግስት “ሸኔ” ራሱን ደግሞ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት” ብሎ በሚጠራው ቡድ እንደሆነ ጠቅሰው ሴቶች እና ህጻናት ህይወታቸውን ያጡበትና የተሰቃዩበት ግድያ ነው ብለዋል፡፡
የድርጅቱ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሴ ሙቼና አሰቃቂ ግድያ ገለልተኛ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጣራት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በምዕራብ ወለጋ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ጉዳት የደረሰባቸውንና የዐይን እማኞችን ማናገሩን ገልጿል፡፡ ድርጅቱ 10 ሰዎችን አናግሮ በጭፍጨፋው በብዛት የተገደሉት ህጻናትና ሴቶች እንደሆኑና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ጭምር እደተገደሉ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከተጎጂዎች ባረጋገጠው መረጃ መሰረት ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ 22 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡
የድርጅቱ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሴ ሙቼና፤ በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እነዚህን ግድያዎች የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ድረስ ሊከታተሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትርጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም በጊምቢው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ብዛት 338 ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን የአማራ ማህበር በአሜሪካ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር ከ 1 ሺ እንደሚልቅ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ከጥቃቱ የተረፉ አንድ አባት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ ምልልስ 22 ቤተሰቦቻቸው መገደላቸውንና ሁሉንም ራሳቸው መቅበራቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ በንጽሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸው እና ወደ ቦታው የጸጥታ ኃይል መሰማራቱን መግለጻቸው ይታወሳል።