ማሊ በባማኮ የተመድ ቃል አቀባይ በ24 ሰዓት ውስጥ ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ አዘዘች
ቃል አቀባዩ በማሊ መንግሥት የታሰሩት የኮቲዲቯር ወታደሮች እንዲለቀቁ በትዊተር ገጹ ጠይቋል
ሀገሪቱ ቃል አቀባዩን ያባረረችው በትዊተር ገጹ ያልተገባ መረጃ አሰራጭቷል በሚል ነው
ማሊ በባማኮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ቃል አቀባይ በ24 ሰዓት ውስጥ ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ አዘዘች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ ከሳምንታት በፊት መፈንቅለ መንግስት ሊፈጽሙ ሲያሴሩ ደርሼባቸዋልሁ በሚል 49 የኮቲዲቯር ወታደሮችን አስራለች።
ጎረቤቷ ኮቲዲቯር በበኩሏ ወታደሮቼ በማሊ ከተመድ ጋር በገባሁት ስምምነት ሰላም በማስከበር ላይ ናቸው ስትል አሳውቃ ነበር።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማሊ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦሊቨር ሳልጋዶ ስለጉዳዩ በትዊተር ገጻቸው ማሊ የኮቲዲቯር ወታደሮችን ከእስር እንድትለቅ ጠይቀዋል።
በዚህ ድርጊት የተበሳጨው እና በኮለኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ወታደራዊ መንግስት ቃል አቀባዩ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ጥሰዋል ሲል ከሷል።
በዚህም ምክንያት ቃል አቀባዩ በ72 ሰዓት ውስጥ ማሊን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
በማሊ መንግስት የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረገችው ኮቲዲቯር ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በሰላም ማስከበር ስራ የተሰማሩ ወታደሮቿ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁላት ጠይቃለች።
ቀደም ሲል ተሰማርተው የነበሩ ወታደሮችን ሊተኩ ነበር የተባለላቸው የኮቲዲቯር ወታደሮች ከአቢጃን ወደ ባማኮ በመጓዝ ላይ እያሉ በአውሮፕላን ማረፊያ በማሊ መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ነው ከሁለት ሳምንት በፊት የታሰሩት።
የማሊ ድርጊት ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለባትን የተበላሸ ግንኙነት የባሰ ሊጎዳው ከመቻሉ ባለፈ የሽብርተኞችን ጥቃት እንዳያሰፋ ተሰግቷል።
የማሊ መንግስት በበኩሉ የኮቲዲቯር ወታደሮች ሳያሳውቁ እና ሳያስፈቅዱ ወደ ባማኮ መምጣታቸውን ጠቅሶ በወታደሮቹ ፓስፖርት ላይ የተጠቀሱት መረጃዎች ትክክለኛነት የሚጎድላቸው እና ቅጥረኛ ወታደሮች የመሆናቸው እድል በመስፋቱ ሊያስራቸው እንደቻለ ገልጿል።
የኮቲዲቯር መንግስትም ወታደሮቹ ወደ ማሊ የተላኩት ከተመድ ጋር በተደረገ ውይይት መሰረት መሆኑን ገልጾ፤ ወታደሮቹ ምንም አይ ነት የጦር መሳሪያ አለመታጠቃቸውን እንዲሁም ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ በሌላ አውሮፕላን መላኩን አስታውቋል።
በተመድ የማሊ ተልዕኮ ቃል አቀባይ የኮቲዲቯር መንግስትን ሀሳብ እንደደገፉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የማሊ ወታደራዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ከተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በወቅቱ በስልክ መወያየታቸውን ገልጸው በሰላም ማስከበር ስም የትኛውም ሀገር የማሊን ሉአላዊነት መጣስ እንደማይችል ተናግረዋል ተብሏል።