አሜሪካዊው ወጣት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለመቀላቀል ወደ ሲናይ በረሃ ሊጓዝ ሲል በቁጥጥር ስር ዋለ
ወጣቱ በሲናይ በረሃ ሰርጥ ውስጥ ወደሚገኝ የሽብር ቡድኑ ካምፕ በመግባት ስልጠና የመውሰድ እቅድ ነበረው
ወጣቱ ጥፋተኛ ከተባለም እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር እና 250 ሺህ ዶላር ገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል
አሜሪካዊው ወጣት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ የሽብር ቡድንን ለመቀላቀል ወደ ግብፅ ሲናይ በረሃ ሊጓዝ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።
በአሜሪካዋ ሲያትል የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዳስታወቀው ወጣቱ በግብፅ ሲናይ በረሃ ሰርጥ ውስጥ የሚገኘውን አይ.ኤስ.አይ.ኤስ የሽብር ቡድንን ለመቀላቀል ተቃርቦ ነበረ ብሏል።
የአሜሪካው ስታር ኤንድ ሰትሪፕስ ድረ ገጽ እንዳስነበበው፤ ዊሊያም የተባለው ወጣት ወደ ግብጽ ካይሮ ለመጓዝ አስፈላጊውን ዝግጅት ጨርሶ ነበር።
ለግብፅ ጉዞው የሚያስፈልገውን ፓስፖርት መያዙን እና አስፈላጊ ዶዝ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶችን መውሰዱንም ነው ድረ ገጹ ያስነበበው።
ወጣቱ ወደ ካይሮ ከተጓዘ በኋላ በግብፅ ሲናይ በረሃ ሰርጥ ውስጥ ወደሚገኝ የሽብር ቡድኑ ካምፕ በመግባት ስልጠና የመውሰድ እቅድ ነበረውም ተብሏል።
ይሁን እንጂ ወደ ካይሮ የሚበር አውሮፕላን ላይ ከመሳፈሩ በፊት ባሳለፍነው አርብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል እንደቻለም ነው የተነገረው።
ዊሊያም የሚባለው ይህ ወጣት ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤ ከሳምንታት በኋላም ተመልሶ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ታዟል።
ወጣቱ ጥፋተኛ ከተባለም እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር እና 250 ሺህ ዶላር ገንዘብ ሊቀጣ እንደሚችልም ነው የተነገረው።