ግለሰቡ እገታውን የፈጸመው ከመንግስት ጋር በነበረው ቁርሾ ምክንያት ነው ተብሏል
ንብረትነቱ የሞሪታኒያ መንግስት የሆነው አውሮፕላን ያገተው ይህ አሜሪካዊ ዜጋ የጸጥታ ሀይሎች ወደ እርሱ ከቀረቡ አውሮፕላኑን እንደሚያጋየው አስጠንቅቋል።
ይህ ግለሰብ ከሞሪታንያ መንግስት ጋር ቁርሾ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን አውሮፕላኑን ያገተው በሀገሪቱ በሚገኘው ኖክቾት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ነው። ግለሰቡ የአቪዬሸን ባለሰልጣናት የበረራ ፈቃድ አንዲሰጡት መናገሩን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ይሁንና የሀገሪቱ ባለስልጣናት አጋቹን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በጥረት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
በዚህ አሜሪካዊ ዜጋ የታገተው ይህ አውሮፕላን መንገደኞችን ያላሰፈረ ሲሆን በኖክቾት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በእረፍት ላይ እያለ ነው ተብሏል።
የአውሮፕላን እገታ በሞሪታንያ ታሪክ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር በ1990 ከኖክቾት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተነስቶ ወደ ስፔን ሊበር የነበረ አውሮፕላንን ለማገት ተሞክሮ በጸጥታ ሀይሎች ከሽፏል።