በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ “የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አሳስቦኛል”ላሉት ሶማሊ-አሜሪካዊቷ የምክር ቤት አባል ምላሽ ሰጠ
ደብዳቤው በምክር ቤት ተወካይዋ የተጠቀሱት እስረኞች በጦር ኃይሎች ሆስፒታል እየታከሙ እንደሚገኙና የርሃብ አድማውን እንዳቋረጡ የሚጠቅስ ሲሆን በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉም ይላል
ኤምባሲው “ሊያሳስብዎት የሚገባ ምንም ነገር የለም” ባለበት የደብዳቤ ምላሹ ኢልሃን ዑመር ሁኔታውን በወጉ እንዲያጤኑ ጠይቋል
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያን በተመለከተ “ሊያሳስብዎት የሚገባ ምንም ነገር የለም” ሲል በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የሚነሶታ ተወካይ ኢልሃን ዑመር ምላሽ ሰጠ፡፡
ሶማሊ-አሜሪካዊቷ የምክር ቤት አባል ኢልሃን “ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ በብዙ መልኩ እጅግ የሚያሳስብ ነው”ሲሉ ከትናንት በስቲያ አርብ መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡
በመግለጫው በርሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ ስለሚባልላቸው ፖለቲከኞች የአያያዝ ሁኔታ እና በትግራይ ስለተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ያነሱ ሲሆን ሁኔታውን “በቅርበት እየተከታተሉ” እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በአምባሳደር ፍጹም አረጋ ፊርማ በአድራሻቸው የተጻፈው ደብዳቤም ለዚህ የምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡
“ሊያሳስብዎት የሚገባ ምንም ነገር እንደሌለ ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ” ሲል የሚጀምረው ደብዳቤው በ“እውነታውኛ እና ተጨባጭ በሆነ ትክክለኛ መንገድ” ሁኔታዎችን መመርመሩ ስጋታቸውን ሊያቀል እና በሚዛናዊነት እንዲረዱ ሊያግዝ እንደሚችል ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሁሉም እስረኞች መብቶች እንዲከበሩ በሚያዙ ዓለም አቀፍ መርሆዎች እና ድንጋጌዎች መሰረት ሁሉም ታራሚዎች አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን ያለ ልዩነት በነጻ እንዲያገኙ ለማድረግ በመስራት ላይ ይገኛልም ነው የሚለው፡፡
በምክር ቤት ተወካይዋ የተጠቀሱት እስረኞች በጦር ኃይሎች ሆስፒታል እየታከሙ እንደሚገኙና የርሃብ አድማውን እንዳቋረጡም ይጠቅሳል፡፡
በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉም ነው የሚለው ደብዳቤው፡፡
ደብዳቤው በትግራይ ስለተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የሚያብራራም ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሰብዓዊ ድጋፎች ቅድሚያ እንደሰጡና ከዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ያትታል፡፡
አምባሳደር ፍጹም “ህወሓት በመሰረተ ልማቶች ላይ በፈጸመው ከፍተኛ ውድመት” ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፎችን በቶሎ ለማድረስ ችግሮች እንደነበሩ አልሸሸጉም፡፡
ሆኖም መሰረተ ልማቶቹ በቶሎ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ በመደረጉ ወሳኝ የሚባሉ የክልሉ አካባቢዎች ወደ ቀደመ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ “መንግስት ሰብዓዊ ጥሰቶችን ለመመርመር እና ተጠርጣዎችን በህግ ለመጠየቅ ቁርጠኛ ነው” ያሉም ሲሆን ማይካድራን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥሰቶች እየተመረመሩ እንደሆነና የወንጀሉ ፈጻሚዎች ሁሉ በህግ እንደሚጠየቁ ነው ያስቀመጡት፡፡
መንግስት መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሓዊ ለማድረግ “ቁርጠኛ ነው”ም ብለዋል አምባሳደር ፍጹም፡፡
በአካል አለበለዚያም በበይነ መረብ አግኝተው በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ሊገልጹላቸው እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
በቀለ ገርባን ጨምሮ ስለ ሌሎች እስረኞች የአያያዝ ሁኔታ ስለ ሰብዓዊ ድጋፎችና ተያያዥ ጉዳዮች ያላቸውን ስጋት የገለጹት ኢልሃን ዑመር ሚኒያፖሊስንና አካባቢውን መወከል የጀመሩት እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ ነው፡፡
በሚነሶታ እና በአካባቢው አሁን በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኘውን ጃዋር መሃመድን ጨምሮ በርካታ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሌዎች እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡