ፕሬዘዳንት ባይደን መካከለኛ ገቢ ያላቸው አሜሪካዊያንን ህይወት እንደሚቀይሩ ቃል ገቡ
ፕሬዘዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከ200 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን የኮቪድ-19 ክትባት ወስደዋል
የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ሁሉም አሜሪካዊያን የሚተማመኑበት ተቋም እንዲሆን መሰራት አለበትም ብለዋል
ፕሬዘዳንቱ ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ 100ኛ ቀናቸውን አስመልክቶ ለተወካዮች ምክር ቤት ንግግር አድርገዋል።
46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፕሬዚዳንታዊ ሥራቸውን የጀመሩበትን መቶኛ ቀን ምክንያት በማድረግ ለተወካዮች ምክር ቤቱ ጥምር ጉባዔ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ለሰራተኞች እና መካከለኛ ኢኮኖሚ ላላቸው አሜሪካዊያንን ህይወት የሚቀይሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ፕሬዘዳንት ባይደን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኢኮኖሚ ዓለምን መምራቱን እንዲቀጥል የሚያደርጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር በተለይም የቻይናን ተጽዕኖ ለመገዳደር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ለበርካታ አሜሪካዊያን የስራ እድል በመፍጠር በታሪክ ትልቁን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩም ፕሬዘዳንቱ ቃል ገብተዋል።
በተለይም የዜጎች የገቢ አለመመጣጠን ክፍተትን ለመሙላት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ የተናገሩት ባይደን ትሪሊዮን ዶላር በማውጣት አለመመጣጠኑን እንደሚያጠቡም ተናግረዋል።
ባይደን የአሜሪካ መንገዶችን እና የባቡር መስመሮችን ለመጠገን ማቀዳቸውን የተናገሩ ሲሆን በ1.8 ትሪሊዮን ዶላር በቀጥታ ለዜጎች እርዳታ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
በገጠር የሚኖሩ አሜሪካዊያን የ35 በመቶ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ አደርጋለሁም ብለዋል ፕሬዘዳንት ባይደን በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግራቸው።ባይደን አክለውም በ21ኛው መቶ ከፍለ ዘመን ተወዳዳሪ ለመሆን የቻይናን እና የሌሎች አገራትን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አብዮት መብለጥ ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።
ሲኤንኤን በሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት 53 በመቶ አሜሪካዊያን ባይደን ስራቸውን በሚገባ እያከናወኑ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን ከ10ሩ አሜሪካዊያን ደግሞ 6ቱ ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል በመፈጸም ላይ እንደሆኑ ያምናሉ ተብሏል።
ባይደን ወደ ሰልጣን ከመጡበት ቀን አንስቶ ባለፉት 100 ቀናት ውስጥ 200 ሚሊዮን አሜሪካዊያን የኮሮና ቫይረስ ክትባታቸውን ወስደዋል።
ይሁንን ባይደን አሁንም ቢሆን አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ያለው የስደተኞች ቀውስ፤ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊስ መገደል እና ተቋሙን የመለወጥ ጉዳይ ትልቅ ፈተና እንደሆኑበት ለምከር ቤቱ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የፌደራል ፖሊስ እንደገና እንዲደራጅ እና ሁሉም አሜሪካዊያን የሚተማመኑበት ተቋም እንዲሆን እንዲሰሩም ፕሬዘዳንቱ ጠይቀዋል።የፌደራል ፖሊስ ለውጥ የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም ከመካሄዱ በፊት እንዲጠናቀቅም ፕሬዘዳንቱ አሳስበዋል።