22 ልጅና የልጅ ልጆቻቸው የተገደሉባቸው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ
የተገደሉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን እራሳቸው መቅበራቸውንም ነው የተናገሩት

ግድያው በተደረገበት ስፍራ የፌዴራልም ሆነ የክልል ባለስልጣናት እንዳልመጡ ተናግረዋል
አቶ መሀመድ የሱፍ ሙሄ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ዕድሜያቸውን በትክክል እንደማያውቁት ይናገራሉ፡፡
የቶሌ ቀበሌ ነዋሪው አቶ መሐመድ 22 ቤተሰብ በአንድ ቀን እንደተገደለባቸው ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ ከተገደሉባቸው ቤተሰቦቻቸው መካከል ከወለደች አራት ቀን የሆናት እመጫት ልጃቸው አንዷ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ የሱፍ የአራት ቀን እመጫት ልጃቸው ከእነ ልጇ በጥይት መገደሏን ያነሱ ሲሆን፤ ገዳዮቹ ህጻኗን እንኳን አለመተዋቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ ልጆቻቸው ከነልጅ ልጆቻቸው መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን የመጀመሪያና ሶስተኛ ልጆቻቸው እስከ ልጅ ልጆቻቸው አምስት፤ አምስት ሆነው መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛዋ ልጃቸው ከሶስት ልጆቿ ጋር፤ እመጫቷ ልጃቸው ከሁለት ልጆቿ ጋር፤ ሌላኛዋ ልጃቸው ከአንድ ልጇ ጋር እንደተገደሉባቸው አቶ መሐመድ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የተዳረችው የአቶ መሐመድ ልጅ እንዲሁም አንድ ወንድ ልጅም እንደተገደሉባቸው ነው የገለጹት፡፡
አቶ መሐመድ በአጠቃላይ ስድስት ልጆቻቸው እና 16 የልጅ ልጆቻቸው መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን የቀበሯቸውም እራሳቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ አዛውንቱ እናታቸውም አባታቸውም የተገደሉባቸውን ሰባት ልጆች ይዘው እዛው ቶሌ ቀበሌ መቀመጣቸውንና መሸሽ አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ በታጣቂዎች እንደተገደሉባቸው የጠቀሷቸውን ሁሉንም እራሳቸው እንደቀበሩ ገልጸዋል፡፡ ሃዘንተኛው አዛውንት የራሳቸውን ቤተሰቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ 60 ሰዎችን መቅበራቸውን ይናገራሉ፡፡
“የእኔን ልጆችና የልጅ ልጆች የቀበርኩት እኔ ነኝ፤ በእኔ እጅ ነው የተቀበሩት ማንም አልቀበረልኝም፤ እኔ እራሴ ነኝ የቀበርኳቸው” ሲሉም ይናገራሉ አቶ መሐመድ፡፡ ከሟቾች ባለፈም የቆሰሉ ስድስት ልጆች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡ አንደኛዋ ልጃቸው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሄደች ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ የሄደችው ልጃቸውእግሯ ይቆረጥ አይቆረጥ እየተባለ እንደሆነ ያነሱት አዛውንቱ የሟቾችን ስም ዝርዝር መናገር እንደሚችሉም ነው የገለጹት፡፡
የአቶ መሐመድ የሱፍ ሙሄ 22 የቤተሰብ አባላትን ካሳጣቸው ግድያ የተረፉት በቆሎ ማሳ ውስጥ ገብተው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው በቆሎ ማሳ ውስጥ ገብተው የተደበቁት ገዳዮቹ ሴት እና ልጅ “አይገድሉም” በሚል ግምት እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
የአቶ መሐመድ የሱፍ ሙሄ ጓደኛዬ መሐመድ አሊ በበኩላቸው የልጃቸው ሚስት ከነልጇ እንደተገደለች ያነሱ ሲሆን ጓደኛቸው አቶ መሐመድ የሱፍ ግን 22 ቤተሰቦቻቸውን ማጣታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ጥቃት አድራሾቹን ያውቋቸው እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ መሐመድ ከግድያው በፊት ወደ ደምቢዶሎ በቶሌ ቀበሌ ማለፋቸውንና ምግብም ጠይቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ ሲፈጸም ወንዶች በብዛት ወደ ስራ ሄደው እንደነበርአቶ መሀመድ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ እናታቸውና አባታቸው የተገደሉባቸውን ሰባትት ፤ አባታቸው የተገደለባቸው አምስት በድምሩ 12 የልጅ ልጆች ይዘው ግራ በመጋባት መቀመጣቸውን የገለጹት አቶ መሐመድ የፌዴራልም የክልል ባለስልጣናት መጥተው እንዳልጠየቋቸው ተናግረዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ በተፈጸመ ጭፍጨፋ የሟቾች ቁጥር 2 ሺ እንደሚደርስ አቶ መሐመድ ገልጸዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋው ግድያ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ለኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብናደርግም ማግኘት ባለመቻላችን ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
የፈዴራል መንግስት ግድያ በተደረገበት አካባቢ የሕግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች "አሸባሪዎችን ለማጥፋት በጋራ እንሠራለን” ብለዋል፡፡