የህወሓት ተዋጊዎች በአማራ ክልል ፈጽመውታል የተባለው ግድያ እንዲመረመርና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አሜሪካ ጠየቀች
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ አስገድዶ መድፈርን ያካትታል የተባለለትን ግድያ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል
ዋሽንግተን ተዋጊዎቹ በክልሉ ተፈጽሟል በተባለው ግድያ እጅግ ማሰቧን አስታውቃለች
የህወሓት ተዋጊዎች በአማራ ክልል ፈጽመውታል የተባለው ግድያ እጅግ እንዳሳሰባት አሜሪካ አስታወቀች፡፡
ዋሽንግተን በወርሃ ነሃሴ መጨረሻ እና በመስከረም መባቻ ግድም እንደተፈጸሙ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በተደረጉ ጥፋቶች ማሰቧን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስገድዶ መድፈርን ያካትታል የተባለለትን ግድያ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ሁሉም የውጊያው ተዋናዮች በሰላማዊ ዜጎች ላይ በማድረስ ላይ ያሉትን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እና ጥቃት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለችግሩ ዘላቂ እልባት መስጠት ይቻል ዘንድ ለተፈጸመው ግፍ ታማኝነት ያለው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል የሚለው ጽኑ አቋም እንዳለውም አስታውቋል ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው።
ግድያዎች መቀጠላቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች አሁንም መውጣት መቀጠላቸው ለግጭቱ በፍጥነት ማብቂያ ሊበጅለት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ሲልም ገልጿል፡፡
መስሪያ ቤቱ ግጭቱንና ግድያዎችን በማስቆም ሰብዓዊ እርዳታዎችን በተሟላ ሁኔታ ለማድረስና ሰላማዊ የመፍትሔ መንግዶችን ለማፈላለግ ከግጭቱ ተዋናዮች ጋር ተቀራርቦ መስራቱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
አምነስቲ ከሳምንት በፊት ባወጣው የምርመራ ሪፖርት “ህወሓት፤ በአማራ ክልል የጦር ወንጀል መፈጸሙን የሚሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ ነው” ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
በቆቦ እና በጭና አካባቢዎች የተፈጸመ ነው ባለው በዚህ ወንጀል የህወሓት ታጣቂዎች በርካቶችን መግደላቸውን እና የ14 ዓመት ታዳጊዎችን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን መደፈራቸውን አምነስቲ መግለጹም አይዘነጋም፡፡