ጠ/ሚ ዐቢይ በንጹሃን ግድያ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የአብን የምክር ቤት አባላት ጠየቁ
የምክር ቤት አባላቱ ብሔራዊ የሀዘን ቀን መታወጅ እንዳለበት ገልጸዋል
ኦነግ እና መኢአድ በምዕራብ ወለጋ በተፈፀመው ግድያ ላይ መግለጫ አውጥተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ በሚደረገው ግድያ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ አብንን ወክለው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡ አባላት ጠየቁ፡፡
አባላቱ ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ/ም ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ ቢጠይቁም አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ግን ጥያቄውን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ታገሰ “ባልተያዘ አጀንዳ ላይ አንወያይም፤ አጀንዳ ካለ የአማካሪ ኮሚቴ አባል ስለሆኑ በእሱ በኩል እንነጋገራለን” በማለታቸው ስበሰባውን ረግጠው የወጡት የአብን አባላት የባህር ዳር ከተማ ተወካዩ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ የጅጋ ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው፣ የሸበል በረንታ-ዕድ ውሃ ተወካይ አቶ ሙሉቀን አሰፋ እና የጭስ አባይ ተወካዩ አቶ ዘመነ ሃይሉ ናቸው፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አል ዐይን አማርኛ የጠየቃቸው የጅጋ ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው ብሄራዊ የሃዘን ቀን መታወጅ አለበት በሚል አባላቱ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት የተደጋገመው ዘር ተኮር ግድያዎች ከዚህ በኋላ በፍጹም ሊደገም እንደማይገባው የተናገሩት አቶ አበባው መንግስት ለዚህ ማረጋገጫ ይስጥ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ሀገር እንድትቀጥል ከተፈለገ የንጹሃን ህይወት መጥፋት የሚያሳስበው በሙሉ ቆራጥ ውሳኔ ሊወስን ይገባል የሚሉት የምክር ቤት አባሉ የአብን አባላት በንጹሃን ላይ እየተደረገ ያለውን ግድያ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤቱ ተገኝተው ማብራሪያ መስጠት አለባቸው የሚል አቋም እንዳላቸውም ነው የሚገልጹት፡፡
“ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር እንደዚህ አይነት አገራዊ እልቂት ሲፈጠር አፈ-ጉባኤው ከጉባኤው በፊት ከተስብሳቢው የውይይት ሃሳብ ሲነሳ ያስተናግዱ ነበር፤ አሁን ግን የአብን አመራሩንና የም/ቤት አባሉን የዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን ሃሳብ አልቀበልም ማለታቸው ብዙ የምክር ቤት አባላትን እንዳሳዘነ መረጃው አለኝ“ ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
“ጉባኤው በህሊና ጸሎት እንዲጀመር ማድረግ ይቻልም ነበር“ የሚሉት አቶ አበባው፤ ሌላ የምክር ቤት አባል ከአፈ ጉባዔው ጋር በተገናኙ ጊዜ ሊያነሱ ያሰቡትን ሃሳብ ቀድመው አድርሰዋቸው እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡
ሌላው አብንን ወክለው የም/ቤት አባል የሆኑት ሙሉቀን አሰፋ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት ስለዜጎች ግድያ ሙሉ ማብራሪያ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
"እኛ ለህዝባችን እንጅ ለግል ጥቅማችን ፓርላማ አልገባንም ያሉት" አቶ ሙሉቀን በዚህ የአማራ ብሔር ተወላጆች ግድያ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
አል ዐይን አባላቱ ጥያቄያችን በአጀንዳነት አልተያዘም በሚል ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ቀርበው ሊያብራሩ ይገባል መባሉን በተመለከተ አቶ ታገሰ ጫፎን እንዲሁም የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ኃላፊ በስልክ አግኝቶ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በተገኘ ጊዜ ምላሻቸውን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ የተፈፀመውን ጥቃት የተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ አውጥቷል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫው ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ “በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል” መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባ ገልጾ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ወንጀሉን በግልፅ እንዲያወግዝ ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምዕራብ ወለጋ ጥቃት በተሰነዘረበት አካባቢ የመከላከያ ሰራዊት ተሰማርቶ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡